Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ስለ ግብጽ የተነገረ ትንቢት

1 ስለ ግብጽ የተነገረ ንግር፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጻውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።

2 “ግብጻዊውን በግብጻዊው ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድም ወንድሙን፣ ባልንጀራ ባልንጀራውን፣ ከተማም ከተማን፣ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።

3 የግብጻውያን ልብ ይሰለባል፤ ዕቅዳቸውንም መና አስቀራለሁ፤ እነርሱም ጣዖታትንና የሙታንን መናፍስት፣ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ምክር ይጠይቃሉ።

4 ግብጻውያንን አሳልፌ ለጨካኝ ጌታ ክንድ እሰጣቸዋለሁ፤ አስፈሪ ንጉሥም ይገዛቸዋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

5 የአባይ ወንዝ ይቀንሳል፤ ውሃውም እየጐደለ ይሄዳል።

6 መስኖዎቹ ይከረፋሉ፤ የግብጽ ጅረቶች ይጐድላሉ፤ ይጠፋሉም። ደንገሉና ቄጠማውም ይጠወልጋል፤

7 እንዲሁም በአባይ ዳር፣ በወንዙ መፋሰሻ ላይ ያሉት ተክሎች ይጠወልጋሉ። በአባይ ዳር የተዘራው ዕርሻ ሁሉ፣ በነፋስ ይወሰዳል፤ ምንም አይቀርም።

8 ዓሣ አጥማጆች ያዝናሉ፤ በአባይ ወንዝ ላይ መንጠቋቸውን የሚወረውሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ በውሃ ላይ መረባቸውን የሚጥሉ ሁሉ፣ ጕልበታቸው ይዝላል።

9 የተነደፈ የተልባ እግር የሚፈትሉ፣ የተባዘተ ጥጥ የሚሠሩ ሸማኔዎችም ተስፋ ይቈርጣሉ።

10 ልብስ ሠሪዎች ያዝናሉ፤ ደመወዝተኞችም ልባቸው ይሰበራል።

11 የጣኔዎስ አለቆች በጣም ቂሎች ናቸው፤ የፈርዖን ጠቢባን ምክራቸው የማይረባ ነው፤ ፈርዖንን፣ “እኔ ከጥበበኞች አንዱ ነኝ፤ የጥንት ነገሥታትም ደቀ መዝሙር ነኝ” እንዴት ትሉታላችሁ?

12 የእናንተ ጠቢባን አሁን የት አሉ? የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በግብጽ ላይ ያሰበውን ነገር፣ እስኪ ያሳዩአችሁ፤ ያሳውቋችሁም።

13 የጣኔዎስ አለቆች ተሞኝተዋል፤ የሜምፊስ ሹማምት ተታልለዋል፤ የሕዝቧ ዋና ዋናዎች፣ ግብጽን አስተዋታል።

14 እግዚአብሔር የድንዛዜን መንፈስ አፍስሶባቸዋል፤ ሰካራም በትፋቱ ዙሪያ እንደሚንገዳገድ፣ ግብጽንም በምታደርገው ነገር ሁሉ እንድትንገዳገድ አደረጓት።

15 ራስም ይሁን ጅራት፣ የዘንባባ ዝንጣፊም ይሁን ደንገል፣ ለግብጽ የሚያደርጉላት አንዳች ነገር የለም።

16 በዚያ ቀን ግብጻውያን እንደ ሴት ይሆናሉ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ በሚያንቀሳቅሰው ክንዱ ፊት ይፈራሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም።

17 የይሁዳ ምድር በግብጽ ላይ ሽብር ትነዛለች፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ካቀደው የተነሣ፣ ስለ ይሁዳ ወሬ የሰማ ሁሉ ይሸበራል።

18 በዚያ ቀን ዐምስት የግብጽ ከተሞች በከነዓን ቋንቋ ይናገራሉ፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርም ወገን ለመሆን ቃል ኪዳን ይገባሉ፤ ከእነዚህም ከተሞች አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።

19 በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራል፤ በድንበሯም ላይ ለእግዚአብሔር ዐምድ ይቆማል።

20 ይህም በግብጽ ምድር ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቋቸውም የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፣ አዳኝና ታዳጊ ይልክላቸዋል፤ እርሱም ያድናቸዋል።

21 እግዚአብሔር ራሱን ለግብጻውያን ይገልጣል፤ እነርሱም በዚያ ቀን እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ በመሥዋዕትና በእህል ቍርባንም ያመልኩታል። ለእግዚአብሔር ስእለት ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽሙታል።

22 እግዚአብሔር ግብጽን በመቅሠፍት ይመታታል፤ መትቶም፤ ይፈውሳቸዋል። እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።

23 በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር አውራ መንገድ ይዘረጋል፤ አሦራውያን ወደ ግብጽ፣ ግብጻውያንም ወደ አሦር ይሄዳሉ፤ ግብጻውያንና አሦራውያን በአንድነት ያመልካሉ።

24 በዚያ ቀን እስራኤል፣ ከግብጽና ከአሦር ጋራ የምድር በረከት ለመሆን በሦስተኛነት ትቈጠራለች።

25 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርም፣ “ሕዝቤ ግብጽ፣ የእጄ ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告