Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በደማስቆ ላይ የተነገረ ንግር

1 ስለ ደማስቆ የተነገረ ንግር፤ “እነሆ፤ ደማስቆ ከእንግዲህ ከተማነቷ ይቀራል፤ የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።

2 የአሮኤር ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤ የመንጎች መሰማሪያ ይሆናሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም።

3 የተመሸገ ከተማ ከኤፍሬም፣ የመንግሥት ሥልጣን ከደማስቆ ይወርዳል፤ የሶርያም ቅሬታ እንደ እስራኤላውያን ክብር ይሆናል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

4 “በዚያ ቀን የያዕቆብ ክብር ይደበዝዛል፤ የሰውነቱም ውፍረት ይሟሽሻል።

5 ዐጫጅ የቆመውን ሰብል ሰብስቦ፣ ዛላውንም በክንዱ እንደሚያጭድ፣ ይህም በራፋይም ሸለቆ እንደሚለቀም ቃርሚያ ይሆናል።

6 ሆኖም የወይራ ዛፍ ሲመታ፣ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ በቅርንጫፍ ራስ ላይ እንደሚቀር፣ አራት ወይም ዐምስት ፍሬ ችፍግ ባለው ቅርንጫፍ ላይ እንደሚቀር፣ እንዲሁ ጥቂት ቃርሚያ ይተርፋል” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።

7 በዚያ ቀን ሰዎች ወደ ፈጣሪያቸው ይመለከታሉ፤ ዐይኖቻቸውም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ።

8 በእጃቸውም ወደ ሠሯቸው መሠዊያዎች አይመለከቱም፤ በጣቶቻቸው ላበጇቸው የዕጣን መሠዊያዎች፣ ለአሼራም የአምልኮ ዐምዶች ክብር አይሰጡም።

9 በዚያ ቀን በእስራኤል ልጆች ምክንያት የተተዉት ጠንካራ ከተሞች ጥሻና ውድማ እንደ ሆኑ ሁሉ፣ እነዚህ ሁሉ ባድማ ይሆናሉ።

10 አዳኝ አምላክህን ረስተሃል፤ መሸሸጊያ ዐለትህንም አላስታወስህም፤ ስለዚህ ምርጥ ተክል ብትተክልም፣ እንግዳ ዘርንም ብትዘራ፣

11 በተከልህበት ቀን እንዲበቅል፣ በዘራህበትም ማግስት እንዲያብብ ብታደርግ እንኳ፣ መከሩ በደዌና በማይሽር ሕመም ቀን፣ እንዳልነበረ ይሆናል።

12 ወዮ! የብዙ ሕዝቦች የቍጣ ድምፅ እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኻል! አቤት፤ የሰዎች ከፍተኛ ጩኸት እንደ ኀይለኛ ውሃ ያስገመግማል!

13 ሰዎቹ እንደ ኀይለኛ ውሃ ጩኸት ቢያስገመግሙም፣ እርሱ ሲገሥጻቸው፣ በኰረብታ ላይ በነፋስ እንደሚበንን ትቢያ፣ በዐውሎ ነፋስ ፊት እንደሚበተን ገለባ ይበተናሉ።

14 እነሆ፤ ሲመሽ ድንገተኛ ሽብር ሆነ! ከመንጋቱ በፊት ግን አንዳቸውም አልተገኙም። የዘረፉን ዕድል ፈንታ፣ የበዘበዙን ዕጣ ይህ ሆነ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告