ኢሳይያስ 16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ከምድረ በዳው ማዶ ካለችው ከሴላ፣ ለምድሪቱ ገዥ፣ ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ የበግ ጠቦት ግብር ላኩ። 2 ከጐጇቸው ተባርረው ግራ እንደ ተጋቡ ወፎች፣ የሞዓብ ሴቶችም በአርኖን ወንዝ መሻገሪያ እንዲሁ ይሆናሉ። 3 “ምክር ለግሱን፤ ውሳኔ ስጡን፤ በቀትር ጥላችሁን እንደ ሌሊት አጥሉብን፤ የሸሹትን ደብቁ፤ ስደተኞችን አሳልፋችሁ አትስጡ። 4 የሞዓባውያን ስደተኞች ከእናንተ ጋራ ይቈዩ፤ እናንተም ከአጥፊው መጠጊያ ሁኗቸው።” የጨቋኙ ፍጻሜ ይመጣል፤ ጥፋቱ ያከትማል፤ እብሪተኛም ከምድር ገጽ ይጠፋል። 5 ዙፋን በፍቅር ይመሠረታል፤ ከዳዊት ቤት የሆነ፣ በፍርድ ፍትሕን የሚሻ፣ ጽድቅንም የሚያፋጥን፣ አንድ ሰው በታማኝነት በላዩ ይቀመጣል። 6 የሞዓብን መዘባነን፣ እጅግ መታበዩንና ኵራቱን፣ እብሪቱንና ስድነቱን ሰምተናል፤ ትምክሕቱ ግን ከንቱ ነው! 7 ስለዚህ ሞዓባውያን ዋይ ይላሉ፤ በአንድነትም ስለ ሞዓብ ዋይታ ያሰማሉ፤ ስለ ቂርሐራሴት ከተማ ሰዎች ትዝታ፣ በሐዘን ያለቅሳሉ። 8 የሐሴቦን ዕርሻ፣ የሴባማም የወይን ተክል ጠውልጓል፤ የአሕዛብ ገዦች፣ ኢያዜርን ዐልፈው፣ ምድረ በዳውን ዘልቀው፣ ሥሮቻቸውን እስከ ባሕር ሰድደው የነበሩትን የተመረጡ የወይን ተክሎችን ረጋግጠዋል። 9 ስለዚህ ስለ ሴባማ የወይን ተክል፣ ኢያዜር እንዳለቀሰች፣ እኔም አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦን ሆይ፤ ኤልያሊ ሆይ፤ በእንባዬ አርስሻለሁ! ፍሬ ባፈራሽበት ወቅት የነበረው ሆታ፣ መከርሽም ሲደርስ የነበረው ደስታ ተቋርጧልና። 10 ደስታና ሐሤትም ከአትክልቱ ቦታ ተወግዷል፤ በወይን ተክልም ቦታ ዝማሬ የለም፤ እልልታም ቀርቷል። በወይን መጭመቂያ ቦታ የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮችን ሆታ አጥፍቻለሁና። 11 ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ እንደ በገና የሐዘን እንጕርጕሮ ታሰማለች፤ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ ታለቅሳለች፤ 12 ሞዓብ ወደ ኰረብታዋ ብትወጣ፣ ትርፏ ድካም ብቻ ነው፤ ለጸሎት ወደ መቅደሷ ብትገባም፣ ዋጋ የለውም። 13 እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ሞዓብ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 14 አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የተቀጠረ ሠራተኛ ቀን እንደሚቈጥር፣ የሞዓብ ክብርና የሕዝቧ ብዛት በሦስት ዓመት ውስጥ ይዋረዳል፤ የሚቀረውም ሕዝብ ጥቂትና ደካማ ይሆናል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.