ኢሳይያስ 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት 1 ስለ ሞዓብ የተነገረው ንግር ይህ ነው፤ የሞዓብ ዔር ፈራረሰች፤ በአንድ ሌሊትም ተደመሰሰች። የሞዓብ ቂር ፈራረሰች፣ በአንድ ሌሊት ተደመሰሰች። 2 ዲቦን ወደ መቅደሱ ወጣ፤ ሊያለቅስም ወደ ኰረብታው ሄደ፤ ሞዓብ ስለ ናባው፣ ስለ ሜድባም ዋይታ ያሰማል፤ ራስ ሁሉ ተመድምዷል፤ ጢምም ሁሉ ተላጭቷል። 3 በየመንገዱም ማቅ ይለብሳሉ፤ በየሰገነቱና በየአደባባዩ ሁሉም ያለቅሳሉ፤ እንባም ይራጫሉ። 4 ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮኹ፤ ድምፃቸው እስከ ያሀጽ ድረስ ተሰማ፤ ስለዚህ የሞዓብ ጦረኞች ጮኹ፤ ልባቸውም ራደ። 5 ልቤ ስለ ሞዓብ አለቀሰ፤ ስደተኞቿም እስከ ዞዓር፣ እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ሸሹ፤ እንባቸውን እያፈሰሱ ወደ ሉሒት ወጡ፤ በሖሮናይም መንገድም፣ ስለ ጥፋታቸው ዋይ እያሉ ነጐዱ። 6 የኔምሬ ውሆች ደርቀዋል፤ ሣሩ ጠውልጓል፤ ቡቃያውም ጠፍቷል፤ ለምለም ነገር አይታይም። 7 ስለዚህ ያገኙትን ሀብት፣ ያከማቹትን ንብረት ከአኻያ ወንዝ ማዶ ተሸክመው ያሻግሩታል። 8 ጩኸታቸው እስከ ሞዓብ ዳርቻ ድረስ ያስተጋባል፤ ዋይታቸው እስከ ኤግላይም፣ ሰቈቃቸውም እስከ ብኤርኢሊም ደረሰ። 9 የዲሞን ወንዞች በደም ተሞልተዋል፤ በዲሞን ላይ ግን ከዚያ ነገር የበለጠ አመጣለሁ፤ ከሞዓብ በሚሸሹት፣ በምድሪቱም ላይ በሚቀሩት አንበሳ እሰድዳለሁ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.