Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት

1 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ባቢሎን ያየው ንግር፤

2 በተራቈተ ኰረብታ ዐናት ላይ ምልክት ስቀሉ፤ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ፤ በመሳፍንቱም በር እንዲገቡ፣ በእጅ ምልክት ስጡ።

3 በድል አድራጊነቴ ደስ የሚላቸውን ቅዱሳኔን አዝዛለሁ፤ ቍጣዬንም እንዲፈጽሙ፣ ተዋጊዎቼን ጠርቻለሁ።

4 በተራሮች ላይ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ የሚሰማውን ጩኸት አድምጡ፤ በመንግሥታትም መካከል፣ እንደ ተጨናነቀ ሕዝብ ድምፅ የሆነውን ውካታ ስሙ! የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሰራዊቱን ለጦርነት አሰልፏል።

5 እግዚአብሔርና የቍጣው ጦር መሣሪያ፣ ምድሪቱን በሙሉ ለማጥፋት፣ ከሩቅ አገር፣ ከሰማያትም ዳርቻ መጥተዋል።

6 የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና አልቅሱ፤ ሁሉን ቻይ ከሆነ አምላክ ዘንድ ጥፋት ይመጣልና።

7 ስለዚህ እጆች ሁሉ ሽባ ይሆናሉ፤ የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል።

8 ሽብር ይይዛቸዋል፤ ሥቃይና ጭንቀት ይደርስባቸዋል፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ያምጣሉ፤ እርስ በርሳቸው በድንጋጤ ይተያያሉ፤ ፊታቸውም በፍርሀት ቀይ ይሆናል።

9 እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ጨካኝ ነው፤ ምድርን ባድማ ሊያደርጋት፣ በውስጧም ያሉትን ኀጢአተኞች ሊያጠፋ፣ ከመዓትና ከብርቱ ቍጣ ጋራ ይመጣል።

10 የሰማይ ከዋክብትና ሰራዊታቸው፣ ብርሃን አይሰጡም፤ ፀሓይ ገና ከመውጣቷ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።

11 ዓለምን ስለ ክፋቷ፣ ክፉዎችንም ስለ ኀጢአታቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችን እብሪት እሽራለሁ፤ የጨካኞችንም ጕራ አዋርዳለሁ።

12 ሰውን ከነጠረ ወርቅ ይልቅ ውድ፣ ከኦፊርም ወርቅ ይበልጥ ብርቅ አደርጋለሁ።

13 ስለዚህ በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት፣ ቍጣው በሚነድድበት ቀን፣ ሰማያትን እነቀንቃለሁ፤ ምድርንም ከስፍራዋ አናውጣለሁ።

14 እንደሚታደን ሚዳቋ፣ እረኛም እንደሌለው የበግ መንጋ፣ እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል፣ እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።

15 የተማረከ ሁሉ ይወጋል፤ የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።

16 ዐይናቸው እያየ ሕፃናታቸው ይጨፈጨፋሉ፤ ቤታቸው ይዘረፋል፤ ሚስቶቻቸው ይደፈራሉ።

17 እነሆ፤ ለብር ደንታ የሌላቸውን፣ በወርቅም ደስ የማይሰኙትን፣ ሜዶናውያንን አስነሣባቸዋለሁ።

18 ቀስታቸው ጐበዞችን ይፈጃል፤ ሕፃናትን አይምሩም፤ ዐይናቸውም ለልጆች አይራራም።

19 የመንግሥታት ዕንቍ፣ የከለዳውያን ትምክሕት የሆነችውን ባቢሎንን፣ እግዚአብሔር እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ይገለብጣታል።

20 በዘመናት ሁሉ የሚቀመጥባት አይኖርም፤ የሚቀመጥባትም የለም፤ ዐረብ በዚያ ድንኳኑን አይተክልም፤ እረኛም መንጋውን በዚያ አያሳርፍም።

21 ነገር ግን የምድረ በዳ አራዊት በዚያ ይተኛሉ፤ ቀበሮዎች ቤቶቿን ይሞላሉ፤ ጕጕቶች በዚያ ይኖራሉ፤ በበረሓ ፍየል የሚመሰሉ አጋንንትም ይዛለሉበታል።

22 ጅቦች በምሽጎቿ፣ ቀበሮዎችም በተዋቡ ቤተ መንግሥቶቿ ይጮኻሉ፤ ጊዜዋ ቀርቧል፤ ቀኗም አይራዘምም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告