ሆሴዕ 9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበእስራኤል ላይ የሚደርሰው ቅጣት 1 እስራኤል ሆይ፤ ደስ አይበልሽ፤ እንደ ሌሎችም ሕዝቦች ሐሤት አታድርጊ፤ በአምላክሽ ላይ አመንዝረሻልና፤ በየእህል ዐውድማውም ላይ፣ ለጋለሞታ የሚከፈለውን ዋጋ ወድደሻል። 2 የእህል ዐውድማዎችና የወይን መጭመቂያዎች ሕዝቡን አይመግቡም፤ አዲሱም የወይን ጠጅ ይጐድልባቸዋል። 3 በእግዚአብሔር ምድር አይቀመጡም፤ ኤፍሬም ወደ ግብጽ ይመለሳል፤ የረከሰውንም ምግብ በአሦር ይበላል። 4 የወይን ጠጅን ቍርባን ለእግዚአብሔር አያፈስሱም፤ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሠኘውም፤ እንዲህ ዐይነቱ መሥዋዕት ለእነርሱ የሐዘንተኞች እንጀራ ይሆንባቸዋል፤ የሚበሉትም ሁሉ ይረክሳሉ። ይህ ምግብ ለገዛ ራሳቸው ይሆናል፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ አይገባም። 5 በእግዚአብሔር የበዓል ቀናት፣ በዓመት በዓሎቻችሁም ቀን ምን ታደርጋላችሁ? 6 ከጥፋት ቢያመልጡም እንኳ፣ ግብጽ ትሰበስባቸዋለች፤ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች። የብር ሀብታቸውን ዳዋ ያለብሰዋል፤ ድንኳኖቻቸውንም እሾኽ ይወርሳቸዋል። 7 የቅጣት ቀን መጥቷል፤ የፍርድም ቀን ቀርቧል፤ እስራኤልም ይህን ይወቅ! ኀጢአታችሁ ብዙ፣ ጠላትነታችሁም ታላቅ ስለ ሆነ፣ ነቢዩ እንደ ቂል፣ መንፈሳዊውም ሰው እንደ እብድ ተቈጥሯል። 8 ነቢዩ ከአምላኬ ጋራ ሆኖ፣ የኤፍሬም ጠባቂ ነው፤ ዳሩ ግን በመንገዱ ሁሉ ወጥመድ፣ በአምላኩም ቤት ጠላትነት ይጠብቀዋል። 9 በጊብዓ እንደ ነበረው፣ በርኩሰት ውስጥ ተዘፍቀዋል፤ እግዚአብሔር ክፋታቸውን ያስባል፤ ስለ ኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል። 10 “እስራኤልን ማግኘቴ፣ የወይንን ፍሬ በምድረ በዳ የማግኘት ያህል ነበር፤ አባቶቻችሁንም ማየቴ፣ የመጀመሪያውን የበለስ ፍሬ የማየት ያህል ነበር፤ ወደ በኣል ፌጎር በመጡ ጊዜ ግን፣ ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለዩ፤ እንደ ወደዱትም ጣዖት የረከሱ ሆኑ። 11 የኤፍሬም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድ፣ ማርገዝና መፀነስ የለም። 12 ልጆችን ቢያሳድጉ እንኳ፣ ልጅ አልባ እስኪሆኑ ድረስ እነጥቃቸዋለሁ፤ ፊቴን ከእነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣ ወዮ ለእነርሱ! 13 ኤፍሬምን እንደ ጢሮስ፣ በመልካም ስፍራ ተተክሎ አየሁት፤ አሁን ግን ኤፍሬም ልጆቹን፣ ለነፍሰ ገዳዮች አሳልፎ ይሰጣል።” 14 እግዚአብሔር ሆይ፤ ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፉ ማሕፀኖችን፣ የደረቁ ጡቶችን ስጣቸው። 15 “በጌልገላ ካደረጉት ክፋታቸው ሁሉ የተነሣ፣ እኔ በዚያ ጠላኋቸው፤ ስለ ሠሩት ኀጢአት፣ ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም አልወድዳቸውም፤ መሪዎቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ናቸው። 16 ኤፍሬም ተመታ፤ ሥራቸው ደረቀ፤ ፍሬም አያፈሩም፤ ልጆች ቢወልዱም እንኳ፣ ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን እገድላለሁ።” 17 ባለመታዘዛቸው ምክንያት፣ አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተንከራታች ይሆናሉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.