ሆሴዕ 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእስራኤል ዐውሎ ነፋስን ታጭዳለች 1 “መለከትን በአፍህ ላይ አድርግ! ሕዝቡ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና፣ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና፣ ንስር በእግዚአብሔር ቤት ላይ ነው፤ 2 እስራኤልም፣ ‘አምላካችን ሆይ፤ እኛ እናውቅሃለን!’ እያሉ፣ ወደ እኔ ይጮኻሉ። 3 ነገር ግን እስራኤል በጎ የሆነውን ነገር ናቁ፤ ጠላትም ያሳድዳቸዋል። 4 ያለ እኔ ፈቃድ ነገሥታትን አነገሡ፤ እኔንም ሳይጠይቁ አለቆችን መረጡ፤ በብራቸውና በወርቃቸው፣ ለገዛ ጥፋታቸው፣ ጣዖታትን ለራሳቸው ሠሩ። 5 ሰማርያ ሆይ፤ የጥጃ ጣዖትሽን ጣዪ! ቍጣዬ በእነርሱ ላይ ነድዷል፤ የማይነጹት እስከ መቼ ነው? 6 ይህም በእስራኤል ሆነ! የእጅ ጥበብ ባለሙያ የሠራው ይህ ጥጃ፣ አምላክ አይደለም፤ ያ የሰማርያ ጥጃ፣ ተሰባብሮ ይደቅቃል። 7 “ነፋስን ይዘራሉ፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፤ አገዳው ዛላ የለውም፤ ዱቄትም አይገኝበትም፤ እህል አፍርቶ ቢገኝም፣ ባዕዳን ይበሉታል። 8 እስራኤል ተውጠዋል፤ በአሕዛብም መካከል፣ ዋጋ እንደሌለው ዕቃ ሆነዋል። 9 ለብቻው እንደሚባዝን የዱር አህያ፣ ወደ አሦር ሄደዋልና፤ ኤፍሬም በእጅ መንሻ ወዳጅ አበጀ። 10 በአሕዛብ መካከል ራሳቸውን ቢሸጡም፣ እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤ በንጉሥና በአለቆች ጭቈና ሥር፣ እየመነመኑ ይሄዳሉ። 11 “ኤፍሬም ለኀጢአት ማስተስረያ ብዙ መሠዊያዎችን ቢሠራም፣ እነርሱ የኀጢአት መሥሪያ መሠዊያዎች ሆነውበታል። 12 በሕጌ ውስጥ ያለውን ብዙውን ነገር ጻፍሁላቸው፤ እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጠሩት። 13 ለእኔ የሚገባውን መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ሥጋውንም ይበላሉ፤ እግዚአብሔር ግን በእነርሱ አልተደሰተም፤ ስለዚህ ክፋታቸውን ያስታውሳል፤ ኀጢአታቸውን ይቀጣል፤ ወደ ግብጽም ይመለሳሉ። 14 እስራኤል ፈጣሪውን ረሳ፤ ቤተ መንግሥቶችንም ሠራ፤ ይሁዳም የተመሸጉ ከተሞችን አበዛ፤ እኔ ግን በከተሞቻቸው ላይ እሳትን እለቃለሁ፤ ምሽጎቻቸውንም ይበላል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.