ሆሴዕ 6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየእስራኤል ንስሓ አለመግባት 1 “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰባብሮናል፤ እርሱም ይጠግነናል፤ እርሱ አቍስሎናል፤ እርሱም ይፈውሰናል። 2 ከሁለት ቀን በኋላ ያነቃናል፤ በርሱም ፊት እንድንኖር፣ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል። 3 እግዚአብሔርን እንወቀው፤ የበለጠ እናውቀውም ዘንድ አጥብቀን እንከተለው፤ እንደ ንጋት ብርሃን፣ በርግጥ ይገለጣል፤ ምድርን እንደሚያረሰርስ የበልግ ዝናብ፣ እንደ ክረምትም ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።” 4 “ኤፍሬም ሆይ፤ ምን ላድርግህ? ይሁዳ ሆይ፤ ምን ላድርግህ? ፍቅራችሁ እንደ ማለዳ ጉም፣ እንደሚጠፋም የጧት ጤዛ ነው። 5 ስለዚህ በነቢያቴ ቈራረጥኋችሁ፤ በአፌም ቃል ገደልኋችሁ፣ ፍርዴም እንደ መብረቅ በላያችሁ አበራ። 6 ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ አምላክን ማወቅ እወድዳለሁ። 7 እንደ አዳም ቃል ኪዳንን ተላለፉ፤ በዚያም ለእኔ ታማኝ አልነበሩም። 8 ገለዓድ በደም የተበከለች፣ የክፉዎች ሰዎች ከተማ ናት። 9 ወንበዴዎች ሰውን ለማጥቃት እንደሚያደቡ፣ ካህናትም በቡድን እንዲሁ ያደርጋሉ፤ በሴኬም መንገድ ላይ ሰዎችን ይገድላሉ፤ አሳፋሪም ወንጀል ይፈጽማሉ። 10 በእስራኤል ቤት የሚሰቀጥጥ ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ ኤፍሬም ዘማዊ ሆነ፤ እስራኤልም ረከሰ። 11 “ይሁዳ ሆይ፤ ለአንተም፣ መከር ተመድቦብሃል። “ሕዝቤን ከምርኮ አገር በመለስሁ ጊዜ፣ |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.