ሆሴዕ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበእስራኤል ላይ የቀረበ ክስ 1 እናንተ የእስራኤል ልጆች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በምድሪቱ በምትኖሩት ላይ የሚያቀርበው ክስ አለውና፤ ምክንያቱም ታማኝነት የለም፤ ፍቅርም የለም፤ እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድሪቱ የለም። 2 በዚያ ያለው ርግማን፣ መዋሸት፣ መግደል፣ መስረቅና ማመንዘር ብቻ ነው፤ ቃል ኪዳንን ሁሉ ያፈርሳሉ፤ ደም ማፍሰስና ግድያ ይበዛል። 3 ስለዚህ ምድሪቱ አለቀሰች፤ በውስጧም የሚኖሩ ሁሉ ኰሰመኑ፤ የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣ የባሕርም ዓሦች ዐለቁ። 4 “ነገር ግን ማንም ሰው አይከራከር፤ ማንም ሌላውን አይወንጅል፤ በካህናት ላይ ክስን እንደሚያቀርቡ፣ ሕዝብህ እንደዚያው ናቸውና። 5 ቀንና ሌሊት ትደናበራላችሁ፤ ነቢያትም ከእናንተ ጋራ ይደናበራሉ። ስለዚህ እናታችሁን አጠፋታለሁ፤ 6 ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል። ዕውቀትን ስለ ናቃችሁ፣ እኔም ካህናት እንዳትሆኑ ናቅኋችሁ፤ የአምላካችሁን ሕግ ስለ ረሳችሁ፣ እኔም ልጆቻችሁን እረሳለሁ። 7 ካህናት በበዙ ቍጥር በእኔ ላይ የሚያደርጉት ኀጢአት በዝቷል፤ ክብራቸውንም በውርደት ለውጠዋል። 8 የሕዝቤ ኀጢአት ለመብል ሆኖላቸዋል፤ ርኩሰታቸውንም እጅግ ወደዱ። 9 ካህናትም ከሕዝቡ የተለዩ አይደሉም፤ ሁሉንም እንደ መንገዳቸው እቀጣቸዋለሁ፤ እንደ ሥራቸውም እከፍላቸዋለሁ። 10 “ይበላሉ ግን አይጠግቡም፤ ያመነዝራሉ ግን አይበዙም፤ እግዚአብሔርን በመተው፣ ራሳቸውን 11 ለአመንዝራነት፣ ለአሮጌና ለአዲስ የወይን ጠጅ አሳልፈው ሰጡ፤ በእነዚህም የሕዝቤ ማስተዋል ተወሰደ። 12 ከዕንጨት የተሠራውን ጣዖት ምክር ይጠይቃሉ፤ ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል። የአመንዝራነት መንፈስ ያስታቸዋል፤ ለአምላካቸውም ታማኝ አልሆኑም። 13 በተራሮችም ጫፍ ላይ ይሠዋሉ፤ መልካም ጥላ ባለው፣ በወርካ፣ በኮምቦልና በአሆማ ዛፍ ሥር፣ በኰረብቶችም ላይ የሚቃጠል ቍርባን ያቀርባሉ። ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን፣ ምራቶቻችሁም አመንዝራዎች ይሆናሉ። 14 “ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ሲሆኑ፣ የልጆቻችሁም ሚስቶች ሲያመነዝሩ አልቀጣቸውም። ወንዶች ከጋለሞቶች ጋራ ይሴስናሉ፤ ከቤተ ጣዖት ዘማውያን ጋራ ይሠዋሉና፤ የማያስተውል ሕዝብ ወደ ጥፋት ይሄዳል! 15 “እስራኤል ሆይ፤ አንቺ ብታመነዝሪም፣ ይሁዳ በበደለኛነት አትጠየቅ። “ወደ ጌልገላ አትሂዱ፤ ወደ ቤትአዌንም አትውጡ፤ ‘ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብላችሁም አትማሉ። 16 እስራኤላውያን እንደ እልኸኛ ጊደር፣ እልኸኞች ናቸው፤ ታዲያ እግዚአብሔር እነርሱን በመልካም መስክ ውስጥ እንዳሉ የበግ ጠቦቶች እንዴት ያሰማራቸዋል? 17 ኤፍሬም ከጣዖት ጋራ ተጣምሯል፤ እስኪ ተዉት፤ 18 መጠጣቸው ባለቀ ጊዜ እንኳ፣ ዘማዊነታቸውን አያቆሙም፤ ገዦቻቸውም ነውርን አጥብቀው ይወድዳሉ። 19 ዐውሎ ነፋስ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ መሥዋዕቶቻቸውም ኀፍረት ያመጡባቸዋል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.