ዕብራውያን 6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን ወደ ብስለት እንሂድ፤ ከሞተ ሥራ ንስሓ ስለ መግባትና በእግዚአብሔር ስለ ማመን እንደ ገና መሠረትን አንጣል፤ 2 እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣ ስለ ሙታን ትንሣኤና ስለ ዘላለም ፍርድ ትምህርት እንደ ገና አንመሥርት። 3 እግዚአብሔር ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። 4 አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን፣ ሰማያዊውን ስጦታ የቀመሱትን፣ ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች የሆኑትን፣ 5 መልካሙን የእግዚአብሔር ቃልና የሚመጣውን ዓለም ኀይል የቀመሱትን፣ 6 በኋላ ግን የካዱትን እንደ ገና ወደ ንስሓ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም እነርሱ ለገዛ ጥፋታቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደ ገና ይሰቅሉታል፤ ያዋርዱታልም። 7 ዘወትር በርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣና ለሚያርሷትም ፍሬ የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች። 8 ነገር ግን እሾኽና አሜከላ የምታበቅል መሬት ዋጋ ቢስ ትሆናለች፤ መረገሚያዋም ተቃርቧል፤ መጨረሻዋም በእሳት መቃጠል ነው። 9 ወዳጆች ሆይ፤ ምንም እንኳ እንደዚህ ብንናገርም፣ ከድነታችሁ ጋራ የተያያዘ ታላቅ ነገር እንዳላችሁ ርግጠኞች ነን። 10 እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። 11 የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። 12 በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም። የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ርግጠኛነት 13 እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፣ የሚምልበት ከርሱ የሚበልጥ ሌላ ባለመኖሩ፣ በራሱ ማለ፤ 14 እንዲህም አለ፤ “በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ።” 15 አብርሃምም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ የተሰጠውን ተስፋ አገኘ። 16 ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላውም የተባለውን ነገር ስለሚያጸና በመካከላቸው የተነሣው ክርክር ሁሉ ይወገዳል። 17 እግዚአብሔር የማይለወጥ ዐላማውን ለተስፋው ቃል ወራሾች ግልጽ ለማድረግ ስለ ፈለገ፣ በመሐላ አጸናው። 18 እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤ እርሱ በሁለት በማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ወደ እርሱ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንድናገኝ አድርጓል። 19 እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ ከመጋረጃው በስተጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል። 20 ይህም ስፍራ ኢየሱስ ስለ እኛ ቀድሞ የገባበት ነው። እርሱም እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኗል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.