Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዕብራውያን 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ

1 እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት የተሰጠው ተስፋ አሁንም የተጠበቀ ስለ ሆነ፣ ከእናንተ ማንም ለዚያ ሳይበቃ እንዳይቀር እንጠንቀቅ።

2 ለእነዚያ እንደ ተሰበከ ለእኛም ደግሞ ወንጌል ተሰብኮልናልና። ነገር ግን ሰሚዎቹ ቃሉን ከእምነት ጋራ ስላላዋሐዱት አልጠቀማቸውም።

3 እኛ ያመንነው ግን ወደዚያ ዕረፍት እንገባለን፤ እግዚአብሔርም፣ “ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤ ‘ፈጽሞ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም’ ” ብሏል። ይሁን እንጂ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የርሱ ሥራ ተከናውኗል።

4 ስለ ሰባተኛውም ቀን በአንድ ስፍራ፣ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሏልና።

5 ቀደም ባለው ክፍል ደግሞ፣ “ፈጽሞ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም” ይላል።

6 ወደ ዕረፍቱ ገና የሚገቡ አንዳንዶች አሉ፤ ቀድሞ የምሥራቹ ቃል የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ወደ ዕረፍት አልገቡም።

7 ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “ዛሬ” ብሎ እንደ ገና አንድን ቀን ወሰነ፤ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ በዳዊት በኩል፣ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣ ልባችሁን አታደንድኑ” ተብሎ ቀደም ሲል እንደ ተነገረው ነው።

8 ኢያሱ ዕረፍትን ሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ፣ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር።

9 ስለዚህ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ገና ቀርቶለታል፤

10 ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት የሚገባ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱም ደግሞ ከሥራው ያርፋል።

11 እንግዲህ ማንም የእነዚያን አለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ፣ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ።

12 የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።

13 ከእግዚአብሔር ዐይን የተሰወረ ምንም ፍጥረት የለም፤ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው።


ታላቁ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ

14 እንግዲህ ወደ ሰማያት ያረገ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ እምነታችንን አጥብቀን እንያዝ።

15 በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም።

16 እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告