Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሐጌ 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት የተደረገ ጥሪ

1 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል ወደ ይሁዳ ገዥ ወደ ሰላትያል ልጅ ወደ ዘሩባቤልና ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኢዮሴዴቅ ልጅ ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲል መጣ፤

2 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሕዝብ፣ ‘የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ጊዜ ገና ነው’ ይላል።”

3 የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤

4 “ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ፣ እናንተ ራሳችሁ በተዋቡ ቤቶቻችሁ ውስጥ ለመኖር ጊዜው ነውን?”

5 ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስኪ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤

6 ብዙ ዘራችሁ፤ ነገር ግን ያጨዳችሁት ጥቂት ነው። በላችሁ፤ ግን አልጠገባችሁም። ጠጣችሁ፤ ግን አልረካችሁም። ለበሳችሁ፤ ግን አልሞቃችሁም። ደመወዝን ተቀበላችሁ፤ ግን በቀዳዳ ኰረጆ የማስቀመጥ ያህል ነው።”

7 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስኪ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤

8 ወደ ተራራ ውጡ፤ ዕንጨት አምጡ፤ ቤቱን ሥሩ፤ እኔም በርሱ ደስ ይለኛል፤ እከበርበታለሁም” ይላል እግዚአብሔር።

9 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ተስፋ አደረጋችሁ፤ ያገኛችሁት ግን ጥቂት ነው፤ ወደ ቤት ያስገባችሁትንም እኔ እፍ አልሁበት፤ ይህ የሆነው ለምን ይመስላችኋል? የእኔ ቤት ፈርሶ እያለ ሁላችሁም የራሳችሁን ቤት ለመሥራት ስለ ሮጣችሁ ነው፤

10 ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ሰማያት ጠል ከለከሉ፤ ምድርም ፍሬዋን ነሣች።

11 እኔም በዕርሻዎችና በተራሮች፣ በእህሉና በአዲሱ ወይን ጠጅ፣ በዘይቱና ምድር በምታፈራው ሁሉ፣ በሰውና በእንስሳ፣ በእጆቻችሁም ሥራ ላይ ድርቅ አመጣሁ።”

12 ከዚህ በኋላ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፣ ሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፣ ከምርኮ የተረፉትም ሕዝብ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ድምፅ፣ የነቢዩንም የሐጌን መልእክት ሰሙ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ልኮታልና። ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ።

13 ቀጥሎም የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሐጌ፣ ይህን የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እኔ ከእናንተ ጋራ ነኝ” ይላል እግዚአብሔር።

14 ስለዚህ እግዚአብሔር የይሁዳን ገዥ፣ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፣ የሊቀ ካህናቱን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስና ከምርኮ የተረፈውን ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አነሣሣ፤ እነርሱም መጥተው የአምላካቸውን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመሩ።

15 ይህ የሆነውም ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ በሃያ አራተኛው ቀን ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告