ዕንባቆም 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየዕንባቆም ጸሎት 1 በዝማሬ የቀረበ የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት፤ በሺግዮኖት ። 1 በዝማሬ የቀረበ የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት፤ በሺግዮኖት። 2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ዝናህን ሰምቻለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህም አስፈራኝ፤ በእኛ ዘመን አድሳቸው፤ በእኛም ጊዜ እንዲታወቁ አድርግ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን ዐስብ። 3 አምላክ ከቴማን፣ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ መጣ። ሴላ ክብሩ ሰማያትን ሸፈነ፤ ውዳሴውም ምድርን ሞላ። 4 ጸዳሉ እንደ ፀሓይ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጣ፤ ኀይሉም በዚያ ተሰውሯል። 5 መቅሠፍት በፊቱ ሄደ፤ ቸነፈርም እግር በእግር ተከተለው። 6 ቆመ፤ ምድርን አንቀጠቀጠ፤ ተመለከተ፤ ሕዝቦችን አብረከረከ፤ የዘላለም ተራሮች ተፈረካከሱ፤ የጥንት ኰረብቶችም ፈራረሱ፤ መንገዱ ዘላለማዊ ነው። 7 የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ፣ የምድያምም መኖሪያዎች ሲታወኩ አየሁ። 8 እግዚአብሔር ሆይ፤ በወንዞች ላይ ተቈጣህን? መዓትህስ በምንጮች ላይ ነበርን? በፈረሶችህና በድል አድራጊ ሠረገሎችህ በጋለብህ ጊዜ፣ በባሕር ላይ ተቈጥተህ ነበርን? 9 ቀስትህን አዘጋጀህ፤ ፍላጻም እንዲመጣልህ አዘዝህ፤ ሴላ ምድርን በወንዞች ከፈልህ፤ 10 ተራሮች አዩህ፤ ተጨነቁም፤ የውሃ ሞገድ ዐልፎ ሄደ፤ ቀላዩ ደነፋ፤ ማዕበሉንም ወደ ላይ አነሣ። 11 ከሚወረወሩ ፍላጾችህ፣ ከሚያብረቀርቅ የጦርህ ነጸብራቅ የተነሣም፣ ፀሓይና ጨረቃ በቦታቸው ቆሙ። 12 በምድር ላይ በመዓት ተመላለስህ፤ ሕዝቦችንም በቍጣ ረገጥሃቸው። 13 ሕዝብህን ለመታደግ፣ የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤ የክፋትን ምድር መሪ ቀጠቀጥህ፤ ከራስ ጠጕሩ እስከ እግር ጥፍሩም ዕርቃኑን አስቀረኸው። ሴላ 14 እንደ ዐውሎ ነፋስ ሊበታትነን የመጣውን፣ ምስኪኑን በስውር በመዋጥ የሚደሰተውን፣ የሰራዊት አለቃ ራስ፣ በገዛ ጦሩ ወጋህ። 15 ታላላቅ ውሆችን በመናጥ፣ ባሕሩን በፈረሶችህ ረገጥህ። 16 እኔ ሰማሁ፤ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከንፈሬ ከድምፁ የተነሣ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርሀት እስከ ዐጥንቴ ዘልቆ ገባ፤ እግሬም ተብረከረከ፤ ሆኖም በሚወርረን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፣ የጥፋትን ቀን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ። 17 ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣ ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣ ዕርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣ የበጎች ጕረኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣ ላሞችም በበረት ውስጥ ባይገኙ፣ 18 እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። 19 ጌታ እግዚአብሔር ኀይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል። ለመዘምራን አለቃ፣ በባለአውታር መሣሪያዎቼ የተዘመረ መዝሙር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.