ዕንባቆም 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ነቢዩ ዕንባቆም የተቀበለው ንግር፤ የዕንባቆም ማጕረምረም 2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣ አንተ የማትሰማው፣ “ግፍ በዛ” ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው? 3 ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቷል። 4 ስለዚህ ሕግ ደክሟል፤ ፍትሕ ድል አይነሣም፤ ፍትሕ ይጣመም ዘንድ፣ ክፉዎች ጻድቃንን ይከብባሉ። የእግዚአብሔር መልስ 5 “ተመልከቱ፤ ማንም ቢነግራችሁ እንኳ፣ የማታምኑትን ነገር፣ በዘመናችሁ ስለማደርግ፣ ሕዝቡን እዩ፤ እጅግም ተደነቁ። 6 የራሳቸው ያልሆኑትን መኖሪያ ስፍራዎች ለመያዝ፣ ምድርን ሁሉ የሚወርሩትን፣ ጨካኝና ፈጣን የሆኑትን፣ ባቢሎናውያንን አስነሣለሁ። 7 እነርሱም የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው፣ ከራሳቸው ይወጣል። 8 ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች፣ ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው። ፈረሰኞቻቸው በፍጥነት ይጋልባሉ፤ ከሩቅ ስፍራም ይመጣሉ። ነጥቆ ለመብላት እንደሚቸኵል ንስር ይበርራሉ፤ 9 ሁሉም ለዐመፅ ታጥቀው ይመጣሉ። ሰራዊታቸው እንደ ምድረ በዳ ነፋስ ወደ ፊት ይገሠግሣል፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባል። 10 ነገሥታትን ይንቃል፤ በገዦችም ላይ ያፌዛል፤ በምሽግ ሁሉ ላይ ይሥቃል፤ የዐፈር ቍልል ሠርቶም ይይዘዋል። 11 ከዚያም በኋላ እንደ ነፋስ ዐልፎ ይሄዳል፤ ጕልበታቸውን አምላካቸው ያደረጉ በደለኞች ናቸው።” የዕንባቆም ዳግመኛ ማጕረምረም 12 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከቀድሞው ያለህ አይደለህምን? የእኔ አምላክ፣ የእኔ ቅዱስ አትሞትም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲፈርድ ሾመኸዋል፤ ዐለት ሆይ፤ ይቀጣ ዘንድ ሥልጣን ሰጥተኸዋል። 13 ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው፤ አንተ በደልን መመልከት አትችልም፤ ታዲያ፣ አታላዮችን ለምን ትመለከታለህ? ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣ ለምን ዝም ትላለህ? 14 ሰዎችን በባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣ ገዥ እንደሌላቸውም እንደሚርመሰመሱ ፍጥረታት አደረግህ። 15 ሁሉንም በመንጠቆ ያወጣቸዋል፤ በመረቡ ይይዛቸዋል፤ በወጥመዱ ውስጥ ይሰበስባቸዋል፤ በዚህም ይደሰታል፤ ሐሤትም ያደርጋል። 16 ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፤ ለወጥመዱም ያጥናል። በእነርሱ ተዝናንቶ ይኖራልና፤ ምግቡም ሠብቷል። 17 ታዲያ መረቡን ባለማቋረጥ መጣል፣ ሕዝቦችንስ ያለ ርኅራኄ መግደል አለበትን? |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.