ዘፍጥረት 48 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምምናሴና ኤፍሬም 1 ከጥቂት ጊዜ በኋላም፣ “አባትህ ታሟል” ተብሎ ለዮሴፍ ስለ ተነገረው ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። 2 ለያዕቆብ፣ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቷል” ተብሎ በተነገረው ጊዜ፣ እስራኤል ተበረታትቶ ዐልጋው ላይ ተቀመጠ። 3 ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሁሉን ቻይ አምላክ በከነዓን ምድር ሎዛ በምትባል ቦታ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም፤ 4 እንዲህም አለኝ፤ ‘ፍሬያማ አደርግሃለሁ፣ አበዛሃለሁ፣ ለብዙ ሕዝብም ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለሚነሡ ዘሮችህ የዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።’ 5 “ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በግብጽ የወለድሃቸው ሁለቱ ልጆችህ ከእንግዲህ የእኔ ልጆች ሆነው ይቈጠራሉ፤ ሮቤልና ስምዖን ልጆቼ እንደ ሆኑ ሁሉ፣ ኤፍሬምና ምናሴም ልጆቼ ይሆናሉ። 6 ከእነርሱ በኋላ የሚወለዱልህ ልጆች ግን፣ የአንተ ይሁኑ፤ በርስት ድልድላቸው ግን በወንድሞቻቸው ስም ይቈጠራሉ። 7 ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ መልስ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረኝ፣ እናትህ ራሔል በከነዓን ምድር ሞታብኝ ዐዘንሁ። እኔም ወደ ኤፍራታ ማለት ወደ ቤተ ልሔም በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።” 8 እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ፣ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ። 9 ዮሴፍም፣ “እነዚህ እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት። እስራኤልም፣ “አቅርባቸውና ልመርቃቸው” አለ። 10 በዚህ ጊዜ እስራኤል ዐይኖቹ በእርጅና ምክንያት በመድከማቸው አጥርቶ ማየት ይሳነው ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን አባቱ ዘንድ አቀረባቸው፤ አባቱም ስሞ ዐቀፋቸው። 11 እስራኤልም ዮሴፍን፣ “ዐይንህን እንደ ገና አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ልጆችህን ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው። 12 ዮሴፍም ልጆቹን ከእስራኤል ጕልበት ፈቀቅ በማድረግ አጐንብሶ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ። 13 ከዚያም ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ኤፍሬምን ከራሱ በስተቀኝ፣ ከእስራኤል በስተግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተግራ፣ ከእስራኤል በስተቀኝ በኩል አቀረባቸው። 14 እስራኤል ግን ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፤ ግራ እጁንም በቀኝ እጁ ላይ አስተላልፎ በበኵሩ በምናሴ ራስ ላይ አኖረ። 15 ከዚህ በኋላ ዮሴፍን ባረከ፤ እንዲህም አለው፤ “አባቶቼ አብርሃምና ይሥሐቅ በፊቱ የተመላለሱት እግዚአብሔር፣ ለእኔም እስከ ዛሬ ድረስ በዘመኔ ሁሉ እረኛ የሆነኝ አምላክ፣ 16 ከጕዳትም ሁሉ የታደገኝ መልአክ፣ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤ እነርሱም በስሜ፣ በአባቶቼ በአብርሃምና በይሥሐቅ ስም ይጠሩ፤ በምድር ላይ እጅግ ይብዙ።” 17 ዮሴፍ፣ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ማድረጉን ሲያይ ተከፋ፤ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ 18 ዮሴፍም፣ “አባቴ ሆይ፤ እንዲህ አይደለም፤ በኵሩ ይህኛው ስለ ሆነ፣ ቀኝ እጅህን እርሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው። 19 አባቱ ግን፣ “ዐውቃለሁ፤ ልጄ ዐውቃለሁ፤ እርሱም እኮ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሙ ከርሱ ይበልጣል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” ብሎ እንቢ አለው። 20 በዚያ ዕለት ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “በአንተ ስም እስራኤል እንዲህ ብሎ ይመርቃል፤ ‘እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ።’ ” በዚህ ሁኔታም ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው። 21 ከዚህ በኋላ እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቧል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር መልሶ ያገባችኋል። 22 እነሆ በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኋትን ዐምባ ከወንድሞችህ ድርሻ አብልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.