Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፍጥረት 39 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዮሴፍና የጲጥፋራ ሚስት

1 በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፣ ግብጻዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው።

2 እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ።

3 አሳዳሪውም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወለት ባየ ጊዜ፣

4 ዮሴፍ በርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው።

5 ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ፣ እግዚአብሔር የግብጻዊውን ቤት ባረከ፤ የእግዚአብሔርም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ።

6 ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በቀር፣ ማንኛውንም ጕዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤

7 እያደርም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለች፤ አፍ አውጥታም፣ “ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው።

8 እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።

9 በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?”

10 ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጕተውም፣ አልሰማትም፤ ከርሷ ጋራ መተኛት ይቅርና ዐብሯትም መሆን አልፈቀደም።

11 አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም።

12 እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።

13 እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፣

14 የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሯል! ሊተኛኝ ወደ እኔ ገባ፤ እኔም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኽሁ፤

15 ለርዳታ መጮኼን ሲሰማም፣ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።”

16 ጌታውም ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ፣ ልብሱን አጠገቧ አቈየችው።

17 ታሪኩንም እንዲህ ስትል ነገረችው፤ “አንተ ያመጣኸው ዕብራዊ ባሪያ መሣቂያ ሊያደርገን ወዳለሁበት ሰተት ብሎ ገባ፤

18 ታዲያ እኔ ድረሱልኝ ብዬ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።”

19 ጌታውም፣ “ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ታሪክ ሲሰማ ተቈጣ።

20 ጌታውም ዮሴፍን ወስዶ፣ የንጉሥ እስረኞች ወደ ተጋዙበት እስር ቤት አስገባው። ይሁን እንጂ ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ ሁሉ፣

21 እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፤ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው።

22 ስለዚህ የወህኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ።

23 እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ሆኖ ሥራውን ሁሉ ያሳካለት ስለ ነበር፣ የወህኒ ቤት አዛዡ በዮሴፍ ኀላፊነት ሥር ስላለው ስለ ማንኛውም ጕዳይ ሐሳብ አይገባውም ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告