ዘፍጥረት 29 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምያዕቆብ መስጴጦምያ ደረሰ 1 ያዕቆብም ጕዞውን ቀጠለ፤ የምሥራቅም ሰዎች ወደሚኖሩበት ምድር ደረሰ። 2 እዚያም በአንድ ሜዳ ላይ ሦስት የበግ መንጋዎች ተኝተው በነበሩበት አጠገብ የውሃ ጕድጓድ አየ። የበግ መንጋዎቹ የሚጠጡት ከዚሁ ጕድጓድ ሲሆን፣ የጕድጓዱም አፍ ትልቅ የድንጋይ መክደኛ ነበረው። 3 መንጎቹ ሁሉ በጕድጓዱ አጠገብ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ እረኞች ድንጋዩን ያንከባልሉና በጎቹን ውሃ ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን በቦታው መልሰው የጕድጓዱን አፍ ይገጥሙታል። 4 ያዕቆብም እረኞቹን፣ “ወንድሞቼ፤ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ከካራን ነን” አሉት። 5 እርሱም፣ “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን እናውቀዋለን” አሉት። 6 ያዕቆብም፣ “ለመሆኑ ደኅና ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን ደኅና ነው፤ ልጁም ራሔል እነሆ፤ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ናት” አሉት። 7 ያዕቆብም፣ “እንደምታዩት ጊዜው ገና ነው፤ መንጎቹ የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ ታዲያ፣ ለምን በጎቹን አጠጥታችሁ ወደ ግጦሽ አትመልሷቸውም?” አላቸው። 8 እነርሱም፣ “መንጎቹ ሁሉ ተሰብስበው ድንጋዩ ከጕድጓዱ አፍ ካልተንከባለለ በቀር አንችልም፤ ከዚያም በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉ። 9 ያዕቆብ ከእረኞቹ ጋራ በመነጋገር ላይ ሳለ፣ ራሔል፣ እረኛ ነበረችና የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች። 10 ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልን፣ እንዲሁም የአጎቱን የላባን በጎች ሲያይ፣ ወደ ጕድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ አንከባለለ፤ የአጎቱንም በጎች አጠጣ። 11 ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 12 ያዕቆብም የአባቷ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል ነገራት፤ እርሷም ሮጣ ሄዳ ይህንኑ ለአባቷ ነገረችው። 13 ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን እንደ ሰማ ሊቀበለው ፈጥኖ ወጣ። ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ፣ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው። 14 ላባም ያዕቆብን፣ “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ነህ” አለው። ያዕቆብ አንድ ወር ሙሉ ዐብሮት ከተቀመጠ በኋላ፣ ያዕቆብ ልያንና ራሔልን አገባ 15 ላባ ያዕቆብን፣ “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለን አይገባምና ደመወዝህ ምንድን ነው?” አለው። 16 ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር። 17 ልያ ዐይነ ልም ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር። 18 ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው። 19 ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ ዐብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። 20 ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ ለርሷ ካለው ፍቅር የተነሣ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው። 21 ከዚያም ያዕቆብ ላባን፣ “እነሆ፤ የተባባልነው ጊዜ አብቅቷል፤ ስለዚህ ሚስቴን አስረክበኝና የባልና የሚስት ወጋችንን እናድርስ” አለው። 22 ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ ሰርግ አበላ። 23 ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም ዐብሯት ተኛ። 24 ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጥር እንድትሆን ሰጣት። 25 ሲነጋም እነሆ፤ ልያ ሆና ተገኘች፤ ስለዚህም ያዕቆብ ላባን፣ “ምነው፣ እንዲህ ጕድ ሠራኸኝ? ያገለገልሁህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው። 26 ላባም እንዲህ አለው፤ “በአገራችን ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤ 27 ይህን የጫጕላ ሳምንት ፈጽምና ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን።” 28 ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋራ ተሞሽሮ ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ፣ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት፤ 29 ባላ የተባለች አገልጋዩንም ደንገጥር እንድትሆናት ለራሔል ሰጣት። 30 ያዕቆብ ከራሔልም ጋራ ተኛ፤ ራሔልን ከልያ አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያም የተነሣ ሌላ ሰባት ዓመት ላባን አገለገለው። 31 እግዚአብሔር ልያ እንዳልተወደደች ባየ ጊዜ ማሕፀኗን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። 32 ልያ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ “እግዚአብሔር መከራዬን ስለ ተመለከተልኝ፣ ከእንግዲህ ባሌ ይወድደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል አለችው። 33 እንደ ገናም ፀንሳ ወለደች፤ እርሷም “እግዚአብሔር እንዳልተወደድኩ ሰምቶ ይህን ልጅ በድጋሚ ሰጠኝ” አለች። ከዚያም የተነሣ ስምዖን ብላ ጠራችው። 34 አሁንም እንደ ገና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት “ከእንግዲህ ባሌ ያቀርበኛል” አለች፤ ስለዚህ ሌዊ ብላ ጠራችው። 35 እንደ ገና ፀንሳ አሁንም ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” አለች፤ ስሙንም ይሁዳ ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ መውለድ አቆመች። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.