ዘፍጥረት 24 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየይሥሐቅና የርብቃ ጋብቻ 1 በዚህ ጊዜ አብርሃም ሸመገለ፤ ዕድሜውም ገፋ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሁሉ ነገር ባረከው። 2 አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ፣ የቤቱ ሁሉ አዛዥ የሆነውን አረጋዊ አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፤ 3 ልጄን፣ በመካከላቸው ከምኖር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋራ እንዳታጋባው በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር ማልልኝ። 4 ነገር ግን ወደ አገሬ፣ ወደ ገዛ ዘመዶቼ ሄደህ ለልጄ ለይሥሐቅ ሚስት ትፈልግለታለህ።” 5 አገልጋዩም፣ “ሴቲቱ ከእኔ ጋራ ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ምን አደርጋለሁ? ልጅህን አንተ ወደ መጣህበት አገር ልውሰደውን?” ሲል ጠየቀው። 6 አብርሃምም እንዲህ አለው፤ “ምንም ቢሆን ልጄን ወደዚያ እንዳትመልሰው ተጠንቀቅ፤ 7 ከአባቴ ቤት፣ ከትውልድ አገሬ ያወጣኝና፣ ‘ለዘርህ ይህችን ምድር እሰጣለሁ’ ብሎ በመሐላ ተስፋ የገባልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤ ለልጄም ሚስት ከዚያ ታመጣለታለህ። 8 ሴቲቱ ዐብራህ ወደዚህ ለመምጣት ፈቃደኛ ካልሆነች ግን ካስማልሁህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትውሰደው” አለው። 9 ስለዚህም አገልጋዩ እጁን ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች አድርጎ ስለዚህ ጕዳይ ማለለት። 10 አገልጋዩም ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥሩን ወሰደ፤ ምርጥ ምርጡንም ዕቃ ሁሉ ጭኖ፣ የናኮር ከተማ ወደምትገኝበት ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ተጓዘ። 11 እዚያም እንደ ደረሰ፣ ግመሎቹን ከከተማው ውጭ የውሃ ጕድጓድ አጠገብ አንበረከከ፤ ጊዜውም ውሃ ለመቅዳት የሚወጣበት ነበር። 12 ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጕዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው። 13 እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ። 14 እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘ዕንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይሥሐቅ የመረጥሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” 15 እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። 16 ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያላወቃት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች። 17 አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። 18 እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው። 19 እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች። 20 ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጕድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው። 21 አገልጋዩም አንዲት ቃል ሳይናገራት፣ እግዚአብሔር መንገዱን አሳክቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ልጅቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር። 22 ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውየው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣ 23 “ለመሆኑ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኝ እንደ ሆነ፣ እባክሽ ንገሪኝ” ብሎ ጠየቃት። 24 እርሷም፣ “እኔ፣ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችው፤ 25 ደግሞም፣ “በቤታችን በቂ ገለባና ድርቈሽ እንዲሁም ለእናንተ የሚሆን ማደሪያ አለን” አለችው። 26 ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ 27 እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።” 28 ልጅቷ ሮጣ ሄዳ፣ የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተ ሰቦች ነገረች። 29 ርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱም ሰውየው ወዳለበት የውሃ ጕድጓድ ፈጥኖ ሄደ። 30 እኅቱ ያደረገችውን የወርቅ ቀለበትና አምባሮች እንዳየ፣ እንዲሁም ርብቃ ሰውየው ያላትን ስትናገር እንደ ሰማ፣ ወዲያውኑ ወደ ሰውየው ሄደ፤ በምንጩም ዳር ከግመሎቹ አጠገብ ቆሞ አገኘው፤ 31 እርሱንም “አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ ሆይ፤ ና፤ እዚህ ውጭ የቆምኸው ለምንድን ነው? እነሆ፤ ለአንተ ማረፊያ ለግመሎችህም ማደሪያ አዘጋጅቻለሁ” አለው። 32 ሰውየው ከላባ ጋራ ወደ ቤት ሄደ፤ የግመሎቹ ጭነት ተራግፎ ገለባና ድርቈሽ ተሰጣቸው፤ ለርሱና ዐብረውት ለነበሩት ሰዎች የእግር ውሃ ቀረበላቸው። 33 ለሰውየውም ማእድ ቀረበለት፤ እርሱ ግን፣ “የመጣሁበትን ጕዳይ ሳልናገር እህል አልቀምስም” አለ። ላባም፣ “ዕሺ፤ ተናገር” አለው። 34 እርሱም እንዲህ አለ፤ “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ፤ 35 እግዚአብሔር ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ እርሱም በልጽጓል፤ በጎችና ከብቶች፣ ብርና ወርቅ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች፣ ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል። 36 የጌታዬ ሚስት ሣራ በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤ ጌታዬም ያለውን ሀብት ሁሉ ለልጁ ሰጥቶታል። 37 ጌታዬ እንዲህ ሲል አማለኝ፤ ‘ከዚህ ከምኖርበት አገር፣ ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋራ ልጄን አታጋባው፤ 38 ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት፣ ወደ ገዛ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት አምጣለት።’ 39 “እኔም ጌታዬን፣ ‘ሴቲቱ ከእኔ ጋራ ወደዚህ ለመምጣት ባትፈቅድስ?’ ብዬ ጠየቅሁት። 40 “እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁ እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋራ ይልካል፤ ከገዛ ወገኖቼና ከአባቴ ቤት፣ ለልጄ ሚስት እንድታመጣለት መንገድህን ያቃናል። 41 ወደ ወገኖቼ ከሄድህ፣ ከመሐላው የተፈታህ ትሆናለህ፤ እነርሱ እንኳ ልጅቱን አንሰጥም ቢሉህ፣ ከመሐላው ንጹሕ ትሆናለህ’ አለኝ። 42 “እኔም ዛሬ ወደ ውሃው ጕድጓድ ስደርስ እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቃድህ ቢሆን የመጣሁበትን ጕዳይ አቃናልኝ፤ 43 እነሆ፤ በምንጩ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ ውሃ ልትቀዳ የምትመጣውን ኮረዳ፣ “ከእንስራሽ ውሃ አጠጪኝ” ስላት፣ 44 “ዕሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ” የምትለኝ እርሷ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ የመረጣት ትሁን።’ 45 “በልቤ የምጸልየውን ጸሎት ገና ሳልጨርስ፣ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች፤ ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ ቀዳች። እኔም፣ ‘እባክሽ፤ ውሃ አጠጪኝ’ አልኋት። 46 “እርሷም ፈጥና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ፣ ‘ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣለሁ’ አለች። እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቹንም አጠጣች። 47 “ለመሆኑ ‘የማን ልጅ ነሽ’ ብዬ ጠየቅኋት። “እርሷም፣ ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለችኝ። “ከዚያም ቀለበቱን አደረግሁላት፤ አምባሩንም በእጇ አስገባሁላት። 48 ተደፍቼም ለእግዚአብሔር ሰገድሁ፤ ለጌታዬ ወንድም የልጅ ልጅ የሆነችውን ቈንጆ፣ ለጌታዬ ልጅ እንዳገኝለት በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። 49 እንግዲህ አሁን ለጌታዬ በጎነትና ታማኝነት የምታሳዩ ከሆነ ሐሳባችሁን አስታውቁኝ፤ ካልሆነ ግን ቍርጡን ንገሩኝና የምሄድበትን ልወስን።” 50 ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ በዚህም ሆነ በዚያ ምንም ማለት አንችልም። 51 ርብቃ ይቻትልህ፤ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁነው።” 52 የአብርሃም አገልጋይ ያሉትን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ። 53 ከዚያም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ደግሞም ለወንድሟና ለእናቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሰጣቸው። 54 እርሱና ዐብረውት የነበሩ ሰዎችም በልተው፣ ጠጥተው እዚያው ዐደሩ። በማግስቱም ጧት ሲነሡ፣ የአብርሃም አገልጋይ፣ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አለ። 55 ወንድሟና እናቷም፣ “ልጅቷ ከእኛ ጋራ ቢያንስ ዐሥር ቀን ያህል ትቈይና ከዚያ በኋላ ልትሄድ ትችላለች።” ብለው መለሱ። 56 እርሱ ግን፣ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አላቸው። 57 እነርሱም፣ “ለማንኛውም ልጅቱን እንጥራትና ትጠየቅ” አሉ። 58 ስለዚህ ርብቃን ጠርተው፣ “ከዚህ ሰው ጋራ መሄድ ትፈቅጃለሽ?” ሲሉ ጠየቋት። እርሷም፣ “አዎን፤ እሄዳለሁ” አለች። 59 ከዚያም እኅታቸውን ርብቃን ከሞግዚቷ ጋራ፣ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና ዐብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው። 60 ርብቃንም እንዲህ ብለው መረቋት፤ “እኅታችን ሆይ፤ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽ የጠላቶቹን ደጆች ይውረስ”። 61 ከዚያም ርብቃና አገልጋዮቿ ተዘጋጁ፤ ግመሎቻቸውም ላይ ወጥተው ሰውየውን ተከተሉት፤ በዚህ ሁኔታ አገልጋዩ ርብቃን ይዟት ሄደ። 62 በዚህ ጊዜ፣ ይሥሐቅ በኔጌብ ይኖር ስለ ነበር፣ ከብኤርላሃይሮኢ መጥቶ ነበር። 63 ይሥሐቅም አንድ ምሽት ላይ በጥሞና ለመቈየት ወደ መስክ ወጣ አለ፤ ቀና ብሎ ሲመለከትም፣ ግመሎች ከሩቅ ሲመጡ አየ። 64 ርብቃም እንደዚሁ አሻግራ ስትመለከት፣ ይሥሐቅን አየች፤ ከግመልም ወረደች፤ 65 አገልጋዩንም፣ “ይህ ሊገናኘን በመስኩ ውስጥ ወደዚህ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። አገልጋዩም፣ “ጌታዬ ነው” ብሎ መለሰላት፤ እርሷም መሸፈኛዋን ተከናነበች። 66 አገልጋዩም ያደረገውን ሁሉ ለይሥሐቅ ነገረው። 67 ይሥሐቅም ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ፤ አገባት፣ ሚስትም ሆነችው፤ እርሱም ወደዳት። ይሥሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.