Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፍጥረት 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


እግዚአብሔር ለአብራም የገባው ኪዳን

1 ከዚህም በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤ “አብራም ሆይ፤ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ታላቅ ዋጋህም እኔው ነኝ።”

2 አብራምም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ያለ ልጅ የቀረሁ ስለ ሆንሁ፣ የቤቴ ወራሽ የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር ነው፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” አለው።

3 “አንተ ልጆች ስላልሰጠኸኝ፣ ከቤቴ አገልጋይ አንዱ ወራሼ መሆኑ አይቀርም።”

4 በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፤ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል።”

5 ወደ ውጭም አውጥቶ፣ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስኪ መቍጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቍጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል” አለው።

6 አብራም እግዚአብሔርን አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት።

7 ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ይህችን ምድር ላወርስህ፣ ከከለዳውያን ምድር፣ ከዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው።

8 አብራምም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለሁ?” አለ።

9 እግዚአብሔርም “እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት የሆናቸው አንዲት ጊደር፣ አንድ ፍየልና አንድ በግ፣ በተጨማሪም አንድ ዋኖስና አንድ ርግብ ዐብረህ አቅርብልኝ” አለው።

10 አብራምም እነዚህን ሁሉ አቀረበለት፤ ቈርጦም ሁለት ቦታ ከከፈላቸው በኋላ፣ እያንዳንዱን ክፍል በሌላው ወገን ትይዩ አስቀመጠ፤ ወፎችን ግን ለሁለት አልከፈላቸውም።

11 አሞሮችም ሥጋውን ለመብላት ወረዱ፤ አብራም ግን አባረራቸው።

12 ፀሓይ ልትገባ ስትል አብራም እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማ መጣበት።

13 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ እንደሚሆን በርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል።

14 ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እቀጣዋለሁ፤ ከዚያም ብዙ ሀብት ይዘው ይወጣሉ።

15 አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ፤

16 በአራተኛውም ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል፤ የአሞራውያን ኀጢአት ገና ጽዋው አልሞላምና።”

17 ፀሓይ ገብታ ከጨለመ በኋላ የምድጃ ጢስና የሚንበለበል ፋና ታየ፤ በተከፈለውም ሥጋ መካከል ዐለፈ።

18 በዚያ ዕለት እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ሲል ኪዳን ገባለት፤ “ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤

19 የምሰጣቸውም የቄናውያንን፣ የቄኔዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣

20 የኬጢያውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የራፋይምን፣

21 የአሞራውያንን፣ የከነዓናውያንን፣ የጌርጌሳውያንንና የኢያቡሳውያንን ምድር ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告