Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ገላትያ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 እኔ የምለው ይህ ነው፤ ወራሹ ሕፃን እስከ ሆነ ድረስ፣ ሀብት ሁሉ የርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ከባሪያ የተለየ አይደለም።

2 አባቱ እስከ ወሰነለት ጊዜ ድረስ በጠባቂዎችና በሞግዚቶች ሥር ነው።

3 እኛም እንዲሁ ገና ልጆች በነበርንበት ጊዜ፣ ከዓለም መሠረታዊ መንፈሳዊ ኀይሎች ሥር በመሆን በባርነት ተገዝተን ነበር።

4 ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤

5 ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው።

6 ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “አባ፣ አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።

7 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ስለ ሆንህ፣ እግዚአብሔር ወራሽ አድርጎሃል።


ጳውሎስ ስለ ገላትያ ሰዎች ማሰቡ

8 እግዚአብሔርን ከማወቃችሁ በፊት፣ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑት ባሪያዎች ነበራችሁ፤

9 አሁን ግን እግዚአብሔርን ዐውቃችሁታል፤ ይልቁን ደግሞ በእግዚአብሔር ታውቃችኋል። ታዲያ እንደ ገና ወደ ደካማና ወደማይጠቅም ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? ዳግም በርሱ በባርነት ለመጠመድ ትፈልጋላችሁን?

10 ልዩ የሆኑ ቀኖችን፣ ወሮችን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን ታከብራላችሁ!

11 ስለ እናንተ በከንቱ የደከምሁ እየመሰለኝ እፈራላችኋለሁ።

12 ወንድሞች ሆይ፤ እለምናችኋለሁ፤ እኔ እናንተን እንደ መሰልሁ፣ እናንተም እኔን ምሰሉ። እናንተ አንዳች አልበደላችሁኝም።

13 እንደምታውቁት፣ በመጀመሪያ ለእናንተ ወንጌልን የሰበክሁት በሕመም ምክንያት ነበር።

14 ሕመሜ ለእናንተ ፈተና ሆኖባችሁም እንኳ፣ አልሰለቻችሁኝም፤ ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ፣ እንዲያውም እንደ ራሱ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አድርጋችሁ ተቀበላችሁኝ።

15 ለመሆኑ ያ ሁሉ ደስታችሁ የት ደረሰ? ቢቻላችሁ ዐይናችሁን ቢሆን እንኳ አውጥታችሁ የምትሰጡኝ እንደ ነበራችሁ እመሰክራለሁ።

16 እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?

17 እነዚያ ሰዎች ወደ ራሳቸው ሊወስዷችሁ ይተጋሉ፤ ለበጎ ግን አይደለም፤ የሚፈልጉት እናንተን ከእኛ ነጥለው የራሳቸው ሊያደርጓችሁ ነው።

18 ለበጎ እስከ ሆነ ድረስ ተቈርቋሪ መሆን መልካም ነው፤ ይህም መሆን የሚገባው ዘወትር እንጂ እኔ ከእናንተ ጋራ ሳለሁ ብቻ አይደለም።

19 የምወድዳችሁ ልጆቼ ሆይ፤ ክርስቶስ በውስጣችሁ እስኪቀረጽ ድረስ፣ ስለ እናንተ እንደ ገና ምጥ ይዞኛል፤

20 ስለ እናንተ ግራ በመጋባት ተጨንቄአለሁና፤ አሁን በመካከላችሁ ተገኝቼ ለየት ባለ ቋንቋ ልናገራችሁ ምን ያህል በወደድሁ!


አጋርና ሣራ

21 እናንተ ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስኪ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን?

22 አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፏልና።

23 ባሪያ ከነበረችው ሴት የተገኘው ልጅ እንደ ሥጋ ልማድ ነበር፤ ከነጻዪቱ ሴት የተወለደው ግን በተስፋው ቃል መሠረት ነበር።

24 እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች ስለሚያመለክቱ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት።

25 እንግዲህ አጋር በዐረብ አገር ያለችው የሲናን ተራራ በመወከል አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጇ ጋራ በባርነት ናትና።

26 ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት።

27 እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ “አንቺ የማትወልጅ መካን ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣ በእልልታ ጩኺ፤ ባል ካላት ይልቅ፣ የብቸኛዪቱ ልጆች በዝተዋልና።”

28 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ እናንተም እንደ ይሥሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ።

29 በዚያ ጊዜ እንደ ሥጋ ልማድ የተወለደው ልጅ፣ በመንፈስ ኀይል የተወለደውን አሳደደው፤ አሁንም እንደዚያው ነው።

30 ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “ባሪያዪቱን ከነልጇ አባርራት፤ የባሪያዪቱ ልጅ ከነጻዪቱ ልጅ ጋራ አይወርስምና።”

31 ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ የነጻዪቱ እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告