ዕዝራ 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምከዕዝራ ጋራ የተመለሱት የየቤተ ሰቡ አለቆች ስም ዝርዝር 1 በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት ከባቢሎን ዐብረውኝ የወጡት የየቤተ ሰቡ አለቆችና ዐብረዋቸው የተመዘገቡት እነዚህ ናቸው፤ 2 ከፊንሐስ ዘሮች ጌርሶን፤ ከኢታምር ዘሮች ዳንኤል፤ ከዳዊት ዘሮች ሐጡስ፤ 3 እርሱም ከሴኬንያ ዘሮች ነው፤ ከፋሮስ ዘሮች ዘካርያስና ከርሱም ጋራ 150 ወንዶች ተመዝግበው ነበር፤ 4 ከፋሐት ሞዓብ ዘሮች የዘራእያ ልጅ ኤሊሆዔናይና ከርሱም ጋራ 200 ወንዶች፤ 5 ከዛቱ ዘሮች የየሕዚኤል ልጅ ሴኬንያና ከርሱም ጋራ 300 ወንዶች፤ 6 ከዓዲን ዘሮች የዮናታን ልጅ ዔቤድና ከርሱም ጋራ 50 ወንዶች፤ 7 ከኤላም ዘሮች የጎቶልያ ልጅ የሻያና ከርሱም ጋራ 70 ወንዶች፤ 8 ከሰፋጥያስ ዘሮች፣ የሚካኤል ልጅ ዝባድያ፣ ከ80 ወንዶች ጋራ፤ 9 ከኢዮአብ ዘሮች የይሒኤል ልጅ አብድዩና ከርሱ ጋራ 218 ወንዶች፤ 10 ከባኒ ዘሮች የዮሲፍያ ልጅ ሰሎሚትና ከርሱም ጋራ 160 ወንዶች፤ 11 ከቤባይ ዘሮች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ ከርሱም ጋራ 28 ወንዶች፤ 12 ከዓዝጋድ ዘሮች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናንና ከርሱም ጋራ 110 ወንዶች፤ 13 ከአዶኒቃም ዘሮች፣ የመጨረሻዎቹ ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፋላት፣ ይዑኤልና ሸማያ፣ ከእነርሱም ጋራ 60 ወንዶች፤ 14 ከበጉዋይ ዘሮች ዑታይና ዘቡድ፣ ከእነርሱም ጋራ 70 ወንዶች። ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ 15 እኔም ወደ አኅዋ በሚፈስሰው ወንዝ አጠገብ ሰዎቹን ሰበሰብኋቸው፤ በዚያም ሦስት ቀን ቈየን። ሕዝቡንና ካህናቱን ስመለከት፣ ከሌዊ ወገን የሆነ አንድም ሰው በዚያ አላገኘሁም። 16 ስለዚህ መራሕያኑን አልዓዛርን፣ አርኤልን፣ ሸማያን፣ ኤልናታንን፣ ያሪብን፣ ኤልናታን፣ ናታንን፣ ዘካርያስንና ሜሱላምን እንዲሁም መምህራኑን ዮያሪብንና ኤልናታንን አስጠራኋቸው፤ 17 እነርሱንም ካሲፍያ በሚባል ስፍራ አለቃ ወደ ሆነው ወደ አዶ ላክኋቸው፤ በአምላካችን ቤት የሚያገለግሉ ሰዎችን ያመጡልን ዘንድ በካሲፍያ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ለሆኑት ለአዶና ለሥጋ ዘመዶቹ የሚናገሩትን አስታወቅኋቸው። 18 መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በእኛ ላይ ስለ ነበረች፣ ከሞሖሊ ዘሮች የእስራኤል ልጅ የሌዊ ልጅ የሆነውን ሰራብያ ተብሎ የሚጠራውን አስተዋይ ሰው፣ ከርሱም ጋራ ዐሥራ ስምንት የሚሆኑ ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን፤ 19 እንዲሁም ሐሸቢያንና ከሜራሪ ዘሮች የሻያን፣ ከወንድሞቹና ከአጎቶቹ ወንዶች ልጆች ጋራ 20 ወንዶችን አመጡልን። 20 በተጨማሪም ዳዊትና ሹማምቱ ሌዋውያኑን እንዲረዳ ካቋቋሙት ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ቡድን 220 አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየስማቸው ተመዘገቡ። 21 ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጕዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ። 22 “መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቍጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር። 23 ስለዚህ ጾምን፤ ወደ አምላካችንም ስለዚህ ነገር ልመና አቀረብን፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ። 24 እኔም ከካህናት አለቆች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፣ ከእነርሱም ጋራ ሰራብያን፣ ሐሸቢያንና ከወንድሞቻቸውም መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ፤ 25 ንጉሡ፣ አማካሪዎቹ፣ ሹሞቹና በዚያ የነበሩ እስራኤል ሁሉ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን ብር፣ ወርቅና ዕቃ ሁሉ መዝኜ ሰጠኋቸው። 26 ስድስት መቶ ዐምሳ መክሊት ብር፣ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፣ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፣ 27 አንድ ሺሕ ዳሪክ የሚያወጡ ሃያ የወርቅ ወጭቶችና እንደ ወርቅ ነጥረው ከሚያብረቀርቅ ናስ የተሠሩ ሁለት ዕቃዎችን መዝኜ በእጃቸው አስረከብኋቸው። 28 እንዲህም አልኋቸው፤ “እናንተና እነዚህ ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ብሩና ወርቁ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር የበጎ ፈቃድ ስጦታ ነው። 29 ኢየሩሳሌም በሚገኘው በእግዚአብሔር ቤት ክፍሎች ውስጥ በዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ በሌዋውያኑና በየቤተ ሰቡ የእስራኤል አለቆች ፊት እስክትመዝኗቸው ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።” 30 ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ አምላካችን ቤት እንዲሄድ የተመዘነውን ብር፣ ወርቅና ንዋያተ ቅድሳት ተረከቡ። 31 እኛም በመጀመሪያው ወር ዐሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችን እጅ በላያችን ነበረች፤ እርሱም ከጠላቶቻችንና በመንገድ ላይ ከሚሸምቁ አዳነን። 32 ኢየሩሳሌምም ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ዐረፍን። 33 በአራተኛው ቀን ብሩን፣ ወርቁንና ንዋያተ ቅድሳቱን በአምላካችን ቤት መዝነን ለኦርዮ ልጅ ለካህኑ ለሜሪሞት በእጁ አስረከብነው፤ ከርሱም ጋራ የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር፣ ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባትና የቢንዊ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ። 34 ሁሉም ነገር ተቈጠረ፤ ተመዘነም፤ የተመዘነውም ሁሉ በዚያ ጊዜ ተመዘገበ። 35 ከዚያም ከምርኮ የተመለሱት፣ ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችን፣ ዘጠና ስድስት አውራ በጎችን፣ ሰባ ሰባት ተባዕት ጠቦቶችን፣ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኀጢአት መሥዋዕት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን አቀረቡ። ይህም ሁሉ ለእግዚአብሔር የቀረበ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበር። 36 የንጉሡንም ትእዛዝ ለንጉሡ እንደራሴዎችና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚገኙት አገረ ገዦች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት ረዱ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.