ዕዝራ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምቤተ መቅደሱ እንዳይሠራ የተነሣ ተቃውሞ 1 የይሁዳና የብንያም ጠላቶች ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ሲሰሙ፣ 2 ወደ ዘሩባቤልና ወደ ቤተ ሰቡ አለቆች መጥተው፣ “እኛም እንደ እናንተ አምላካችሁን የምንፈልግ ነን፤ የአሦር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ካመጣን ጊዜ ጀምሮ ለርሱ ስንሠዋለት ቈይተናል፤ ስለዚህ ዐብረን ከእናንተ ጋራ እንሥራ” አሏቸው። 3 ዘሩባቤል፣ ኢያሱና ሌሎቹ የእስራኤል ቤተ ሰቦች አለቆች ግን፣ “ለአምላካችን ቤተ መቅደስ እንድትሠሩ ከእኛ ጋራ የሚያገናኛችሁ ምንም ነገር የለም። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ ባዘዘን መሠረት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የምንሠራው እኛ ብቻ ነን” ሲሉ መለሱላቸው። 4 ከዚያም የምድሪቱ ነዋሪዎች የይሁዳን ሕዝብ ተስፋ ማስቈረጥና ሥራውንም እንዳይቀጥሉ ማስፈራራት ጀመሩ። 5 ከፋርስ ንጉሥ ከቂሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ዕቅዶቻቸውን የሚያሰናክሉ መካሪዎችን በገንዘብ ገዙባቸው። በጠረክሲስና በአርጤክስስ ዘመን የተደረገ ሌላው ተቃውሞ 6 በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የጽሑፍ ክስ መሠረቱባቸው። 7 በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፣ ሚትሪዳጡ፣ ጣብኤልና ተባባሪዎቹ ወደ አርጤክስስ ደብዳቤ ጻፉ። ደብዳቤው የተጻፈው በአራማይክ ፊደል፣ በአራማይክ ቋንቋ ነበረ። 8 አገረ ገዥው ሬሁምና ጸሓፊው ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፤ 9 ደብዳቤው የተጻፈው፣ ከአገረ ገዥው ሬሁም፣ ከጸሓፊው ሲምሳይ በትሪፖሊስ፣ በፋርስ፣ በአርክ፣ በባቢሎን እንዲሁም በሱሳ ማለትም በኤላማውያን ላይ ዳኞችና ገዦች ከሆኑት ከተባባሪዎቻቸው፣ 10 ደግሞም ታላቁና ኀያሉ አስናፈር አፍልሶ በሰማርያ ከተማና ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲሰፍሩ ካደረጋቸው ሌሎች ሕዝቦች ነው። 11 የላኩለት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤ ለንጉሥ አርጤክስስ፣ በኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ከሚኖሩት አገልጋዮችህ የተላከ፤ 12 ከአንተ ዘንድ ወደ እኛ የመጡት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ዐመፀኛና ርኩስ ከተማ እንደ ገና በመሥራት ላይ ናቸው፤ ቅጥሮቿንም እንደ ገና በመሥራትና መሠረቶቿንም በመጠገን ላይ መሆናቸው በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። 13 ከዚህም በላይ ይህች ከተማ ከተሠራች፣ ቅጥሮቿም እንደ ገና ከተገነቡ፣ ቀረጥና እጅ መንሻ ወይም ግብር እንደማይከፍሉ፣ የቤተ መንግሥቱም ገቢ እንደሚቀንስ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። 14 አሁንም እኛ ስለ ቤተ መንግሥቱ ስለሚገደን፣ የንጉሡም ክብር ሲነካ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው፣ ይህ ነገር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ እንዲሆን ይህን መልእክት ልከናል፤ 15 ስለዚህ በአባቶችህ ቤተ መዛግብት ምርመራ ይደረግ፤ በእነዚህ መዛግብት ውስጥ ይህች ከተማ ዐመፀኛ ከተማ እንደ ሆነች፣ ነገሥታትንና አውራጃዎችን የጐዳችና ከጥንት ጀምሮ የዐመፅ ጐሬ ስለ መሆኗ ማስረጃ ታገኛለህ፤ እንግዲህ ከተማዪቱ የተደመሰሰችው በዚህ ምክንያት ነው። 16 ይህች ከተማ ተመልሳ የምትሠራና ቅጥሮቿም እንደ ገና የሚገነቡ ከሆነ፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ምንም ነገር እንደማይኖርህ፣ ንጉሥ ታውቅ ዘንድ እንወድዳለን። 17 ንጉሡም ይህን መልስ ላከ፤ ለአገረ ገዥው ሬሁም፣ ለጸሓፊው ሲምሳይ፣ በሰማርያና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚኖሩ ተባባሪዎቻቸው፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ 18 የላካችሁልኝ ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነብቧል። 19 እኔም ትእዛዝ ሰጥቼ ምርመራ ተደርጓል፤ በምርመራውም መሠረት ይህች ከተማ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታት ላይ ስታምፅ የኖረች የዐመፅና የወንጀል መናኸሪያ እንደ ሆነች ማስረጃ ተገኝቷል። 20 ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ ማዶ ያለውን አገር ሁሉ የገዙ፣ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻም ይቀበሉ የነበሩ ኀያላን ነገሥታት ነበሯት። 21 አሁንም እኔ ትእዛዝ እስከምሰጥበት ድረስ ይህች ከተማ እንደ ገና እንዳትሠራ ሥራውን ያቆሙ ዘንድ ለእነዚህ ሰዎች ትእዛዝ አስተላልፉ። 22 ይህን ነገር ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ በነገሥታቱ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ለምን እየበዛ ይሄዳል? 23 የንጉሡ የአርጤክስስ ደብዳቤ ቅጅ በሬሁም፣ በጸሓፊው በሲምሳይና በተባባሪዎቻቸው ፊት እንደ ተነበበ፣ ወዲያውኑ በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት አይሁድ ሄደው ሥራውን እንዲያቆሙ አስገደዷቸው። 24 ስለዚህም በኢየሩሳሌም የሚሠራው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ሁለተኛ ዓመት ድረስ ተቋረጠ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.