Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ፍጻሜው ደረሰ

1 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ፍጻሜ! በአራቱም የምድሪቱ ማእዘን ፍጻሜ መጥቷል!

3 አሁንም መጨረሻሽ ደርሷል፤ ቍጣዬን በአንቺ ላይ አፈስሳለሁ፤ እንደ አካሄድሽ እፈርድብሻለሁ፤ ስለ ጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ፣ ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ።

4 በርኅራኄ ዐይን አልመለከትሽም፤ ምሕረትም አላደርግልሽም፤ ስለ አካሄድሽና በመካከልሽ ስላለው ጸያፍ ተግባር፣ ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’

5 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘መዓት! ተሰምቶ የማይታወቅ መዓት ይመጣል።

6 ፍጻሜ መጥቷል! ፍጻሜ መጥቷል! በአንቺ ላይ ተነሣሥቷል፤ እነሆ፤ ደርሷል!

7 እናንተ በምድሪቱ የምትኖሩ ሆይ፤ የጥፋት ፍርድ መጥቶባችኋል፤ ጊዜው ደርሷል፤ በተራሮች ላይ እልልታ ሳይሆን ሽብር የሚሰማበት ቀን ቀርቧል።

8 እነሆ፤ መዓቴን በቅርብ ቀን አፈስስብሻለሁ፤ በአንቺ ላይ ቍጣዬን እፈጽምብሻለሁ፤ እንደ አካሄድሽ እፈርድብሻለሁ፤ ስለ ጸያፍ ተግባርሽም ሁሉ ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ።

9 በርኅራኄ ዐይን አልመለከትሽም፤ ምሕረት አላደርግልሽም፤ ስለ አካሄድሽና በመካከልሽ ስላለው ጸያፍ ተግባር፣ ተገቢውን ቅጣት እከፍልሻለሁ፤ በዚያ ጊዜ፣ የምቀሥፍ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።

10 “ ‘እነሆ ቀኑ ይኸው ደረሰ! የጥፋት ፍርድ ተገልጧል፤ በትሩ አቈጥቍጧል፤ ትዕቢት አብቧል።

11 ዐመፅ ዐድጋ የክፋት በትር ሆነች፤ ከሕዝቡ አንድም አይተርፍም፤ ከሰዎቹ፣ ከሀብታቸውና እርባና ካለው ነገር አንዳች አይቀርም።

12 ጊዜው ደርሷል፤ ቀኑም ይኸው! መዓት በሕዝቡ ሁሉ ላይ ስለ መጣ፣ የሚገዛ አይደሰት፤ የሚሸጥም አይዘን።

13 ሁለቱ በሕይወት እስካሉ ድረስ ሻጩ የሸጠውን መሬት አያስመልስም፤ ስለ መላው ሕዝብ የተነገረው ራእይ አይለወጥምና። ከኀጢአታቸው የተነሣ ሕይወቱን ማትረፍ የሚችል አንድም አይገኝም።

14 “ ‘መለከት ቢነፉም፣ ሁሉንም ነገር ቢያዘጋጁም፣ ወደ ጦርነት የሚሄድ አንድ እንኳ አይኖርም፤ መዓቴ በሕዝብ ሁሉ ላይ መጥቷልና።

15 በውጭ ሰይፍ፣ በውስጥ ደግሞ ቸነፈርና ራብ አለ፤ በገጠር ያሉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በከተማ ያሉትም በራብና በቸነፈር ያልቃሉ።

16 ተርፈው ያመለጡት ሁሉ በሸለቆ እንደሚኖሩ ርግቦች ስለ ኀጢአታቸው እያለቀሱ በተራራ ላይ ይሆናሉ።

17 እጅ ሁሉ ይዝላል፤ ጕልበት ሁሉ ውሃ ይሆናል።

18 ማቅ ይለብሳሉ፤ ሽብርም ይውጣቸዋል። ፊታቸው ኀፍረት ይለብሳል፤ ራሳቸውም ይላጫል።

19 “ ‘ብራቸውን በየጐዳናው ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም እንደ ርኩስ ነገር ይቈጠራል። በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ በኀጢአት እንዲወድቁ ዕንቅፋት ሆኖባቸዋልና በልተው አይጠግቡበትም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉበትም።

20 በውብ ዕንቋቸው ታብየዋል፤ ይህንም አስጸያፊ የጣዖት ምስሎቻቸውንና ርኩስ ቅርጻ ቅርጾችን ለመሥራት ተጠቅመውበታል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ወደ ርኩሰት እለውጥባቸዋለሁ።

21 ለባዕዳን ዝርፊያ፣ ለምድር ክፉዎችም ብዝበዛ አድርጌ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ያረክሱታል።

22 ፊቴን ከእነርሱ እመልሳለሁ፤ እነርሱም የከበረውን ቦታዬን ያረክሳሉ፤ ወንበዴዎች ይገቡበታል፤ ያረክሱታልም።

23 “ ‘ምድር በደም መፋሰስ፣ ከተማዪቱም በዐመፅ ተሞልታለችና ሰንሰለት አዘጋጅ።

24 እጅግ የከፉትን ከአሕዛብ አምጥቼ ቤቶቻቸውን እንዲነጥቁ አደርጋለሁ፣ የኀያላኑንም ትዕቢት አጠፋለሁ፤ መቅደሳቸውም ይረክሳል።

25 ሽብር በመጣ ጊዜ ሰላምን ይሻሉ፤ ነገር ግን አያገኟትም።

26 ጥፋት በጥፋት ላይ፣ ወሬም በወሬ ላይ ይመጣል። ራእይን ከነቢይ ለማግኘት ይጥራሉ፤ የሕግ ትምህርት ከካህኑ፣ ምክርም ከሽማግሌው ዘንድ ይጠፋል።

27 ንጉሡ ያለቅሳል፤ መስፍኑ ተስፋ መቍረጥን ይከናነባል፤ የምድሪቱም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች። የእጃቸውን እከፍላቸዋለሁ፤ ራሳቸው ባወጡት መስፈርት መሠረት እፈርድባቸዋለሁ። “ ‘በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告