ሕዝቅኤል 6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምስለ እስራኤል ተራሮች የተነገረ ትንቢት 1 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አዙር፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤ 3 እንዲህም በል፤ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፤ ለገደላገደሎችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል፤ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ የማምለኪያ ኰረብቶቻችሁን አጠፋለሁ። 4 መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሰባበራሉ፤ የታረዱ ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ። 5 የእስራኤላውያንን ሬሳ በጣዖቶቻችሁ ፊት አጋድማለሁ፤ ዐጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ። 6 መሠዊያዎቻችሁ እንዲፈራርሱና እንዲወድሙ፣ ጣዖቶቻችሁ እንዲሰባበሩና እንዲደቅቁ፣ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁ እንዲንኰታኰቱ፣ የእጆቻችሁም ሥራ እንዲደመሰስ፣ የምትኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ ማምለኪያ ኰረብቶችም እንዳልነበሩ ይሆናሉ። 7 የታረዱ ሰዎቻችሁ በመካከላችሁ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8 “ ‘በአሕዛብ መካከል ስትበተኑ፣ አንዳንዶቻችሁ ከሰይፍ ታመልጣላችሁና፣ ጥቂት ሰዎችን አስቀራለሁ። 9 እነዚህ ከሰይፍ የተረፉት፣ ከእኔ ዘወር ባለ አመንዝራ ልባቸውና ጣዖትን በተከተለ አመንዝራ ዐይናቸው የቱን ያህል እንዳሳዘኑኝ፤ በአሕዛብ ምድር ሆነው ያስታውሱኛል፤ ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ርኩስ ተግባር ሁሉ የተነሣም ራሳቸውን ይጸየፋሉ። 10 እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህንም ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ ብዬ የተናገርሁት በከንቱ አይደለም። 11 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ቤት ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ጸያፍ ተግባራቸው ሁሉ የተነሣ በሰይፍ በራብና በቸነፈር ይወድቃሉና፤ በእጅህ እያጨበጨብህ በእግርህም መሬት እየረገጥህ፣ “ወየው!” ብለህ ጩኽ። 12 በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፤ በቅርብ ያለው በሰይፍ ይወድቃል፤ በሕይወት የተረፈውና የዳነው በራብ ያልቃል። መዓቴንም በዚህ ዐይነት ሁኔታ በእነርሱ ላይ እፈጽማለሁ። 13 የታረዱት ሰዎቻቸው በመሠዊያው ዙሪያ በጣዖቶቻቸው መካከል፣ ከፍ ባሉ ኰረብቶች ሁሉና በተራሮች ዐናት ሁሉ ላይ፣ በለመለመ ዛፍ ሁሉና ቅጠሉ በበዛ ወርካ ሁሉ ሥር፣ በአጠቃላይ ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን ባቀረቡበት ስፍራ ሁሉ ተጥለው ሲታዩ፣ ያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 14 እጄን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ የሚኖሩበትንም ስፍራ ከምድረ በዳው እስከ ዴብላታ ድረስ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤ ያን ጊዜም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.