ሕዝቅኤል 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “አንተም፤ የሰው ልጅ ሆይ፤ የተሳለ ሰይፍ ወስደህ እንደ ጢም መላጫ ጠጕርህንና ጢምህን ተላጭበት፤ ጠጕሩንም በሚዛን ከፋፍል። 2 የከበባው ጊዜ ሲፈጸም የጠጕሩን ሢሶ በከተማው ውስጥ አቃጥለው፤ ሌላውን ሢሶ ጠጕር በከተማዪቱ ዙሪያ ሁሉ በሰይፍ ቈራርጠው፤ የቀረውንም ሢሶ ደግሞ ለነፋስ በትነው፤ እኔም በተመዘዘ ሰይፍ አሳድዳቸዋለሁና። 3 ደግሞም ከጠጕሮቹ ጥቂት ወስደህ በመጐናጸፊያህ ጫፍ ቋጥር፤ 4 እንደ ገናም ከእነዚህ ጥቂት ወስደህ እሳት ውስጥ ጨምራቸው፤ አቃጥላቸውም። እሳትም ከዚያ ወጥቶ ወደ እስራኤል ቤት ሁሉ ይሠራጫል። 5 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አገሮችን በዙሪያዋ ሁሉ አድርጌ፣ በአሕዛብም መካከል ያስቀመጥኋት ኢየሩሳሌም ይህች ናት። 6 እርሷም በዙሪያዋ ካሉት አገሮችና አሕዛብ ይልቅ በሕጌና በሥርዐቴ ላይ በክፋቷ ዐመፀች፤ ሕጌን ጥላለች፤ ሥርዐቴንም አልተከተለችም።’ 7 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብ ይልቅ ሞገደኞች ሆናችኋል፤ ሥርዐቴን አልተከተላችሁም፤ ለሕጌም አልታዘዛችሁም። በዙሪያችሁ የሚገኙ አሕዛብ የሚጠብቁትን ሕግ እንኳ አልጠበቃችሁም።’ 8 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ፤ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በአሕዛብም ፊት ፍርድ አመጣብሻለሁ። 9 በጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ ምክንያት ካሁን ቀደም ያላደረግሁትን፣ ወደ ፊትም የማላደርገውን በአንቺ ላይ አደርጋለሁ። 10 ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን፣ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አመጣብሻለሁ፤ ከአንቺ የተረፉትንም ለነፋስ እበትናለሁ።’ 11 ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ መቅደሴን በረከሱ ምስሎችሽና በጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ ስላጐደፍሽ፣ ፊቴን ከአንቺ እመልሳለሁ፤ በርኅራኄ አልመለከትሽም፤ አልምርሽም። 12 ከሕዝብሽ ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፤ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሌላው ሢሶ ከቅጥርሽ ውጪ በሰይፍ ይወድቃል፤ የቀረውን ሢሶ ደግሞ ለነፋስ እበትናለሁ፤ በተመዘዘም ሰይፍ አሳድደዋለሁ። 13 “ከዚያም ቍጣዬ ይበርዳል፤ በእነርሱ ላይ የመጣው መቅሠፍቴ ይመለሳል፤ ስበቀላቸው እረካለሁ፤ በእነርሱም ላይ መዓቴን ካወረድሁ በኋላ፣ እኔ እግዚአብሔር በቅናት እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ። 14 “በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ መካከል፤ በአጠገብሽም በሚያልፉ ሁሉ ፊት ባድማና መሣለቂያ አደርግሻለሁ። 15 በቍጣና በመዓት፣ እንዲሁም በጭካኔ ፍርድ በማመጣብሽ ጊዜ፣ በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ ዘንድ የመሣቂያና የመሣለቂያ፣ የተግሣጽና የማስደንገጫ ምልክት ትሆኛለሽ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ። 16 የሚገድለውንና አጥፊ የሆነውን የራብ ፍላጻ በእናንተ ላይ በምወረውርበት ጊዜ በርግጥ ላጠፋችሁ እሰድዳለሁ። በራብ ላይ ራብ አመጣባችኋለሁ፤ የምግብ ምንጫችሁንም አደርቃለሁ። 17 ራብንና የዱር አራዊትን እሰድድባችኋለሁ፤ እነርሱም ልጅ አልባ ያደርጓችኋል። ቸነፈርና ደም መፋሰስ ያጥለቀልቃችኋል፤ ሰይፍንም አመጣባችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.