Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 47 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ከቤተ መቅደሱ ተነሥቶ የሚፈውስ ወንዝ

1 ከዚያም ያ ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ መልሶ አመጣኝ፤ ከቤተ መቅደሱ መድረክ ሥር ውሃ እየወጣ፣ ወደ ምሥራቅ ይፈስስ ነበር፤ ቤተ መቅደሱ ለምሥራቅ ትይዩ ነበርና። ውሃው ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ በኩል፣ በመሠዊያው ደቡብ በኩል፣ ሥር ሥሩን ይወርዳል።

2 ከዚያም በሰሜኑ በር በማውጣት በውጭ አዙሮ በምሥራቅ አቅጣጫ ወዳለው የውጭ በር መራኝ፤ ውሃውም በደቡብ በኩል ይፈስስ ነበር።

3 ያም ሰው የመለኪያውን ገመድ በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ በመሄድ፣ አንድ ሺሕ ክንድ ለካ፤ ከዚያም እስከ ቍርጭምጭሚት በሚደርሰው ውሃ ውስጥ መራኝ፤

4 ቀጥሎም አንድ ሺሕ ክንድ ለካ፤ እስከ ጕልበት ወደሚደርስም ውሃ መራኝ፤ ከዚያም ሌላ አንድ ሺሕ ክንድ ለካ፤ እስከ ወገብ ወደሚደርስም ውሃ መራኝ።

5 እንደ ገናም አንድ ሺሕ ክንድ ለካ፤ አሁን ግን ልሻገረው የማልችል ወንዝ ሆነ፤ ምክንያቱም ውሃው ስለ ሞላና ጥልቅ ስለ ነበረ፣ በዋና ካልሆነ በቀር በእግር ሊሻገሩት የማይቻል ነበረ።

6 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን ታየዋለህን?” ሲል ጠየቀኝ። ከዚያም መልሶ ወደ ወንዙ ዳር መራኝ፤

7 እዚያም በደረስሁ ጊዜ፣ በወንዙ ግራና ቀኝ ብዙ ዛፍ አየሁ።

8 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ይህ ውሃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይፈስሳል፤ ወደ ባሕሩ ወደሚገባበት ወደ ዓረባ ይወርዳል፤ ወደ ባሕሩም ሲፈስስ፣ በዚያ የነበረው ውሃ ንጹሕ ይሆናል።

9 ወንዙ በሚፈስስበት ስፍራ ሁሉ ብዙ ሕያዋን ፍጥረታት ይኖራሉ። ይህ ውሃ በዚያ ስለሚፈስስና ጨውማ የሆነውን ውሃ ንጹሕ ስለሚያደርገው፣ ዓሣ በብዛት ይኖራል፤ ስለዚህ ወንዙ በሚፈስስበት ስፍራ ሁሉ ማንኛውም ነገር በሕይወት ይኖራል።

10 ዓሣ አጥማጆች በወንዙ ዳር ይቆማሉ፤ ከዓይንጋዲ እስከ ዓይንኤግላይም ድረስ ያለው ቦታ መረብ መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣውም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣ፣ የተለያየ ዐይነት ይሆናል።

11 ነገር ግን ረግረጉና ዕቋሪው ውሃ ንጹሕ አይሆንም፤ ጨው እንደ ሆነ ይቀራል።

12 በወንዙም ዳርና ዳር፣ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶች ሁሉ ይበቅላሉ፤ ቅጠላቸው አይደርቅም፤ ፍሬ አልባም አይሆኑም። ከመቅደሱ የሚወጣው ውሃ ስለሚፈስላቸው በየወሩ ያፈራሉ፤ ፍሬአቸው ለምግብ፣ ቅጠላቸውም ለፈውስ ይሆናል።”


የምድሪቱ ወሰን

13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ የምታከፋፍሉባቸው ወሰኖች እነዚህ ናቸው፤ ዮሴፍ ሁለት ዕጣ ይኑረው።

14 እኩል አድርጋችሁ ከፋፍሉት፤ ለቀድሞ አባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ በተዘረጋች እጅ ስለ ማልሁ፣ ምድሪቱ ርስታችሁ ትሆናለች።

15 “የምድሪቱ ወሰን ይህ ነው፤ “በሰሜን በኩል ከታላቁ ባሕር አንሥቶ በሔትሎን መንገድ በሐማት መተላለፊያ አድርጎ እስከ ጽዳድ ይደርሳል፤

16 ከዚያም ቤሮታን፣ በደማስቆና በሐማት ወሰን መካከል ያለውን ሲብራይምን ዐልፎ፣ በሐውራን ወሰን ላይ እስካለው እስከ ሐጸርሃቲኮን ይዘልቃል።

17 ወሰኑ ከባሕሩ በመነሣት፣ በሰሜኑ የደማስቆ ድንበር አድርጎ፣ የሐማትንም ዳርቻ ወደ ሰሜን ትቶ እስከ ሐጸርዔናን ይዘልቃል።

18 በምሥራቅ በኩል ወሰኑ በሐውራንና በደማስቆ መካከል፣ በገለዓድና በእስራኤል ምድር መካከል ዮርዳኖስ ይሆናል፤ የምሥራቁ ድንበር እስከ ምሥራቁ ባሕር ይወርድና እስከ ታማር ይዘልቃል፤ ይህም የምሥራቁ ወሰን ይሆናል።

19 በደቡብ በኩል ወሰኑ ከታማር ይነሣና እስከ መሪባ ቃዴስ ውሃ ይደርሳል፤ ከዚያም የግብጽን ደረቅ ወንዝ ተከትሎ እስከ ታላቁ ባሕር ይዘልቃል፤ ይህ የደቡቡ ወሰን ነው።

20 በምዕራቡ በኩል ወሰኑ ከሐማት መግቢያ ፊት ለፊት እስካለው ቦታ ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል፤ ይህም የምዕራቡ ወሰን ይሆናል።

21 “እነሆ፤ ይህችን ምድር በእስራኤል ነገድ ቍጥር ልክ ትከፋፈላላችሁ፤

22 ለራሳችሁ፣ በመካከላችሁ ለሚኖሩት ልጆች ላሏቸው መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ መድቡ፤ እነርሱንም እንደ እስራኤል ተወላጆች ቍጠሯቸው፤ እንደ እናንተ ከእስራኤል ነገዶች ርስት ይመደብላቸው።

23 መጻተኛ በማንኛውም ነገድ መካከል ቢቀመጥ፣ በዚያ ርስቱን ስጡት፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告