ሕዝቅኤል 45 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየምድሪቱ አከፋፈል 1 “ ‘ምድሪቱን ርስት አድርጋችሁ በዕጣ በምትከፋፈሉበት ጊዜ፣ ርዝመቱ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ሺሕ ክንድ የሆነውን አንዱን ክፍል፣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስፍራ አድርጋችሁ ስጡ፤ ስፍራውም በሙሉ ቅዱስ ይሆናል፤ 2 ከዚሁም ዐምስት መቶ ክንድ በዐምስት መቶ ክንድ፣ ዙሪያው ዐምሳ ክንድ ባዶ ቦታ ቀርቶ፣ ለመቅደሱ ይሁን። 3 ከተቀደሰውም ስፍራ ላይ ርዝመቱ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ፣ ወርዱም ዐሥር ሺሕ ክንድ ለካ፤ በዚህም ውስጥ መቅደሱ፣ ይኸውም ቅድስተ ቅዱሳኑ ይሆናል። 4 ይህም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሚያገለግሉና፣ በእግዚአብሔር ፊት ለአገልግሎት ለሚቀርቡ ካህናት፣ ቅዱስ የሆነ የምድሪቱ ክፍል ይሆናል። 5 ርዝመቱ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ፣ ወርዱ ዐሥር ሺሕ ክንድ ስፋት ያለው ስፍራ መኖሪያ ከተሞቻቸውን እንዲከትሙ በቤተ መቅደስ ለሚያገለግሉ ሌዋውያን ርስት ይሆናል። 6 “ ‘ከተቀደሰው ስፍራ ጋራ የተያያዘ ወርዱ ዐምስት ሺሕ ክንድ፣ ርዝመቱ ሃያ ዐምስት ሺሕ ክንድ የሆነ ቦታ ለከተማዪቱ ርስት አድርገህ ስጥ፤ ይህም ለመላው የእስራኤል ቤት ይሆናል። 7 “ ‘ገዥው ከቅዱሱ ስፍራና ከከተማው ወሰን ግራና ቀኝ ርስት ይኖረዋል፤ ይህም ከምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ምሥራቅ በመዝለቅ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያለውን ወሰን ርዝመት ተከትሎ ለአንዱ ነገድ ከተሰጠው ርስት ጋራ ጐን ለጐን ይሄዳል። 8 ይህም መሬት በእስራኤል ምድር የገዢው ርስት ይሆናል። ከእንግዲህ ገዥዎቼ ሕዝቤን አይጨቍኑም፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት በየነገዳቸው ርስት እንዲይዙ ይፈቅዱላቸዋል። 9 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 10 ትክክለኛ ሚዛን ትክክለኛ ኢፍና ትክክለኛ ባዶስ ይኑራችሁ። 11 የኢፍና የባዶሱ መመዘኛ ተመሳሳይ ይሁን፤ አንድ ባዶስ የሆሜር አንድ ዐሥረኛ እንዲሁም አንድ ኢፍ የሆሜር አንድ ዐሥረኛ ይሆናል፤ ሆሜር ለሁለቱም ሚዛኖች መደበኛ መለኪያ ነው። 12 አንድ ሰቅል ሃያ ጌራህ የሚይዝ ይሆናል፤ በሃያ ሰቅል ላይ ሃያ ዐምስት ሰቅልና ዐሥራ ዐምስት ሰቅል ሲጨመር አንድ ምናን ይሆናል። ልዩ ልዩ መሥዋዕትና በዓላት 13 “ ‘የምታቀርቡት ልዩ መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ሆሜር መስፈሪያ ስንዴ አንድ ስድስተኛ ኢፍ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሆሜር ገብስ አንድ ስድስተኛ ኢፍ ነው። 14 ዘይቱ በባዶስ ሲለካ፣ የተወሰነው መስፈሪያ ከእያንዳንዱ ሆሜር አንድ ዐሥረኛ ባዶስ ይሆናል፤ ይኸውም ዐሥር ባዶስ ወይም አንድ ሆሜር ነው፤ ዐሥር ባዶስ ከአንድ ሆሜር ጋራ እኩል ነውና። 15 እንዲሁም ውሃ ከጠገበው ከእስራኤል መሰማሪያ፣ ሁለት መቶ በግ ካለው ከእያንዳንዱ መንጋ አንድ በግ ይውሰድ። ይህ ሁሉ ለሕዝቡ ማስተስረያ ለሚሆነው ለእህል ቍርባን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለኅብረት መሥዋዕት ይውላል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16 የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይህን ልዩ መባ ለእስራኤል ገዥ ይሰጣሉ። 17 በበዓላት፣ በወር መባቻና በሰንበታት፣ ለእስራኤል ቤት በተወሰኑት በዓላት ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን ማቅረብ የገዢው ኀላፊነት ነው፤ ለእስራኤል ቤት ማስተስረያ እንዲሆንም የኀጢአት መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ያቀርባል።’ 18 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ፤ መቅደሱንም አንጻው። 19 ካህኑም ከኀጢአቱ መሥዋዕት ደም በመውሰድ በቤተ መቅደሱ በር መቃኖች፣ በመሠዊያው ላይኛው ዕርከን አራት ማእዘንና በውስጠኛው አደባባይ በር መቃኖች ላይ ይርጨው። 20 አንድ ሰው ሳያስብ ወይም ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፤ ወር በገባ በሰባተኛው ቀን ይህን ታደርጋለህ፤ በዚህ ዐይነት ለቤተ መቅደሱ ታስተሰርያላችሁ። 21 “ ‘በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታከብራላችሁ፤ ይህም ለሰባት ቀን የሚከበር ሲሆን በዚያ ጊዜ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ትበላላችሁ። 22 በዚያም ቀን ገዥው ስለ ራሱና ስለ ምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ አንድ ወይፈን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል። 23 በዓሉ በሚከበርበት በሰባቱ ቀን ገዥው በየዕለቱ እንከን የሌለባቸውን ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ በየዕለቱም ለኀጢአት መሥዋዕት አውራ ፍየል ያቅርብ። 24 ለአንዱ ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ፣ ለአንድ አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቍርባን አድርጎ፣ ለእያንዳንዱም ኢፍ አንድ የሂን መስፈሪያ ዘይት ዐብሮ ያቅርብ። 25 “ ‘በሰባተኛው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን በሚጀመረው በሰባቱ ቀን በዓል፣ ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ ለእህል ቍርባንና ለዘይቱም እንዲሁ ያቅርብ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.