ሕዝቅኤል 32 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምስለ ፈርዖን የወጣ ሙሾ 1 በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን ሙሾ አውርድ፤ እንዲህም በለው፤ “ ‘አንተ በሕዝቦች መካከል እንደ አንበሳ፣ በባሕሮችም ውስጥ እንደ አስፈሪ አውሬ ነህ፤ በወንዞችህ የምትንቦጫረቅ፣ ውሃውን በእግርህ የምትመታ፣ ምንጮችን የምታደፈርስ ነህ። 3 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ብዙ ሕዝብ ይዤ፣ መረቤን በላይህ ላይ እጥላለሁ፤ በመረቤም ጐትተው ያወጡሃል። 4 በምድር ላይ እጥልሃለሁ፤ ሜዳም ላይ እዘረጋሃለሁ፤ የሰማይ ወፎች ሁሉ እንዲሰፍሩብህ አደርጋለሁ፤ የምድር አራዊት ሁሉ በመስገብገብ ይበሉሃል። 5 ሥጋህን በተራሮች ላይ እበታትነዋለሁ፤ የተረፈውንም በየሸለቆው እሞላዋለሁ። 6 እስከ ተራሮች ባለው መንገድ ሁሉ፣ በሚፈስሰው ደምህ ምድሪቱን አርሳታለሁ፤ ሸለቆዎችም በሥጋህ ይሞላሉ። 7 አንተን በማጠፋ ጊዜ ሰማያትን እሸፍናለሁ፤ ከዋክብታቸውንም አጨልማለሁ፤ ፀሓይን በደመና እሸፍናለሁ፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም። 8 በሰማይ የሚያበሩትን ብርሃናት ሁሉ፣ በአንተ ላይ አጨልማለሁ፤ በምድርህ ላይ ጨለማን አመጣለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9 በማታውቀው ምድር፣ በሕዝቦች መካከል ያንተን ጥፋት ሳመጣ፣ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ። 10 ሕዝቦች በአንተ ላይ ከደረሰው የተነሣ እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤ ሰይፌን በፊታቸው ስነቀንቅ፣ በአንተ ላይ ከደረሰው ሁኔታ የተነሣ ንጉሦቻቸው ይንቀጠቀጣሉ። አንተ በምትወድቅበት ቀን፣ እያንዳንዳቸው ስለ ራሳቸው ሕይወት በመፍራት፣ በየቅጽበቱ ይርበደበዳሉ። 11 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “ ‘የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ፣ በአንተ ላይ ይመጣል። 12 ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ ጨካኝ በሆኑት፣ በኀያላን ሰዎች ሰይፍ፣ ያከማቸኸው ሰራዊት እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤ የግብጽን ኵራት ያንኰታኵታሉ፤ የሰራዊቷም ብዛት ይጠፋል፤ 13 ብዙ ውሃ ባለበት አጠገብ ያለውን፣ የከብት መንጋዋን አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህ የሰው እግር አይረጋግጠውም፤ የከብትም ኰቴ አያደፈርሰውም። 14 ከዚያም ውሆቿን አጠራለሁ፤ ወንዞቿም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 ግብጽን ባድማ ሳደርጋት፣ ምድሪቱም ያላትን ሁሉ ያጣች ስትሆን፣ በዚያም የሚኖሩትን ሁሉ ስመታ፣ ያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ 16 “ስለ እርሷ የሚያወርዱት ሙሾ ይህ ነው፤ የሕዝቦች ሴት ልጆች ያዜሙታል፤ ስለ ግብጽና ስለ ብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” 17 በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ ከወሩም በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 18 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ብዙው የግብጽ ሰራዊት አልቅስ፤ እርሷንና የኀያላንን ሕዝቦች ሴት ልጆች ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋራ ከምድር በታች አውርዳቸው። 19 እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንተ ከሌሎች የተለያችሁ ናችሁን? ውረዱ፤ ባልተገረዙትም መካከል ተጋደሙ።’ 20 እነርሱም በሰይፍ ከተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ሰይፉ ተመዝዟል፤ ከብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ጋራ ትጐተት። 21 በመቃብርም ውስጥ ኀያላኑ መሪዎች ስለ ግብጽና ስለ ተባባሪዎቿ፣ ‘ወደ ታች ወርደዋል፤ በሰይፍ ከተገደሉትና ካልተገረዙትም ጋራ በአንድ ላይ ተጋድመዋል’ ይላሉ። 22 “አሦር ከመላው ሰራዊቷ ጋራ በዚያ ትገኛለች፤ በሰይፍ በወደቁባትና በታረዱባት ሰዎች ሁሉ መቃብር ተከብባለች። 23 መቃብራቸው በጥልቁ ጕድጓድ ውስጥ ነው፤ ሰራዊቷም በመቃብሯ ዙሪያ ተረፍርፏል። በሕያዋን ምድር ሽብርን የነዙ ሁሉ ታርደዋል፤ በሰይፍም ወድቀዋል። 24 “ኤላም በዚያ አለች፤ ሰራዊቷም ሁሉ በመቃብሯ ዙሪያ አለ፤ ሁሉም ታርደዋል፤ በሰይፍ ወድቀዋል። በሕያዋን ምድር ሽብር የነዙ ሁሉ ሳይገረዙ ከምድር በታች ወርደዋል፤ ወደ ጕድጓድ ከወረዱት ጋራ ዕፍረታቸውን ተሸክመዋል፤ 25 በመቃብሯ ዙሪያ ካለው መላው ሰራዊቷ ጋራ፣ በታረዱት መካከል መኝታ ተዘጋጅቶላታል። ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ ሽብራቸው በሕያዋን ምድር ስለ ተነዛ፣ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋራ ዕፍረታቸውን ይሸከማሉ፤ በታረዱትም መካከል ይጋደማሉ። 26 “ሜሼኽና ቶቤል መቃብሮቻቸው በብዙ ሰራዊታቸው መቃብር ተከብበው ይገኛሉ፤ ሁሉም ያልተገረዙ ሲሆኑ፣ በሕያዋን ምድር ሽብራቸውን ስለ ነዙ በሰይፍ ተገድለዋል። 27 ከዘመናት በፊት ከወደቁት ከኀያላን ሰዎች፣ ከእነዚያ ሰይፋቸውን ተንተርሰው፣ ጋሻቸውንም ደረታቸው ላይ ይዘው ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ መቃብር ከወረዱት ጋራ አይጋደሙምን? የእነዚህ ተዋጊዎች ሽብር በሕያዋን ምድር ባሉት ያልተገረዙ ኀያላን ላይ ቢደርስም፣ የኀጢአታቸው ቅጣት በዐጥንታቸው ላይ ይሆናል። 28 “ፈርዖን ሆይ፤ አንተም እንደዚሁ ትሰበራለህ፤ በሰይፍ ከተገደሉት ከእነዚያ ካልተገረዙት ጋራ ትጋደማለህ። 29 “ኤዶምም በዚያ አለች፤ ንጉሦቿና ገዦቿም ሁሉ በዚያ አሉ፤ ኀይል የነበራቸው ቢሆኑም፣ በሰይፍ ከተገደሉት ጋራ ተጋድመዋል፤ ወደ ጕድጓድ ከወረዱት ከእነዚያ ካልተገረዙትም ጋራ ተኝተዋል። 30 “የሰሜን ገዦች በሙሉ፣ ሲዶናውያንም ሁሉ በዚያ ይገኛሉ፤ ከዚህ በፊት በኀይላቸው ምክንያት ሽብር የፈጠሩ ቢሆኑም፣ ከታረዱት ጋራ በኀፍረት ወረዱ፤ ሳይገረዙም በሰይፍ ከተገደሉት ጋራ ይጋደማሉ፤ ወደ ጕድጓድ ከወረዱትም ጋራ ኀፍረታቸውን ይሸከማሉ። 31 “ፈርዖንና ሰራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል፤ በሰይፍ ከተገደለበት ሰራዊትም ሁሉ ሐዘን ይጽናናል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 32 በሕያዋን ምድር ሽብር እንዲያስፋፋ ብፈቅድም እንኳ፣ ፈርዖንና ሰራዊቱ ሁሉ በሰይፍ ከተገደሉት ጋራ ባልተገረዙት መካከል ይጋደማሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.