Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 31 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሊባኖስ ዝግባ

1 በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖንና ስፍር ቍጥር ለሌለው ሕዝቡ እንዲህ በል፤ “ ‘በክብር ከአንተ ጋራ ማን ሊወዳደር ይችላል?

3 ለጫካው ጥላ የሆኑ የሚያማምሩ ቅርንጫፎች የነበሩትን፣ እጅግ መለሎ ሆኖ፣ ጫፉ ሰማይ የደረሰውን፣ የሊባኖስን ዝግባ አሦርን ተመልከት።

4 ውሆች አበቀሉት፤ ጥልቅ ምንጮች አሳደጉት፤ ጅረቶቻቸው ፈሰሱ፤ የሥሮቹንም ዙሪያ ሁሉ አረሰረሱ፤ በመስኩ ላይ ወዳሉት ዛፎች ሁሉ፣ መስኖዎቻቸውን ለቀቁት።

5 ስለዚህ በደን ካሉት ዛፎች ሁሉ፣ እጅግ ከፍ አለ፤ ቅርንጫፎቹ በዙ፤ ቀንበጦቹ ረዘሙ፤ ከውሃውም ብዛት የተነሣ ተስፋፉ።

6 የሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በቅርንጫፎቹ ላይ ጐጇቸውን ሠሩ፤ የምድር አራዊት ሁሉ፣ ከቅርንጫፎቹ ሥር ግልገሎቻቸውን ወለዱ። ታላላቅ መንግሥታትም ሁሉ፣ ከጥላው ሥር ኖሩ።

7 ከተንሰራፉት ቅርንጫፎቹ ጋራ፣ ውበቱ ግሩም ነበር፤ ብዙ ውሃ ወዳለበት፣ ሥሮቹ ጠልቀው ነበርና።

8 በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ ያሉ ዝግባዎች፣ ሊወዳደሩት አልቻሉም፤ የጥድ ዛፎች፣ የርሱን ቅርንጫፎች አይተካከሉትም፤ የኤርሞን ዛፎችም፣ ከርሱ ቅርንጫፎች ጋራ አይወዳደሩም፤ በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ ያለ ማንኛውም ዛፍ፣ በውበት አይደርስበትም።

9 በብዙ ቅርንጫፎች፣ ውብ አድርጌ ሠራሁት፤ በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ፣ በዔድን ያሉትን ዛፎች የሚያስቀና አደረግሁት።

10 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጥቅጥቅ ባለው ቅጠል ላይ ጫፉን ከፍ በማድረግ ራሱን በማንጠራራቱ፣ በርዝማኔውም በመኵራራቱ፣

11 እንደ ክፋቱ መጠን የሥራውን ይከፍለው ዘንድ፣ ለአሕዛብ ገዥ አሳልፌ ሰጠሁት። አውጥቼ ጥዬዋለሁ፤

12 ከአሕዛብ ወገን እጅግ ጨካኝ የሆኑትም ባዕዳን ሰዎች ቈራርጠው ጣሉት። ቀንበጦቹ በተራራዎቹና በሸለቆዎቹ ሁሉ ላይ ወድቀዋል፤ ቅርንጫፎቹም በውሃ መውረጃዎቹ ሁሉ ላይ ተሰባብረው ወድቀዋል፤ የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ከጥላው ሥር በመውጣት ትተዉት ሄደዋል።

13 የሰማይ ወፎች ሁሉ በወደቀው ዛፍ ላይ ሰፈሩ፤ የምድር አራዊት ሁሉ በወደቀው ዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ሰፈሩ።

14 ስለዚህ በውሃ አጠገብ ያለ ማንኛውም ዛፍ፣ ጫፎቹን ችምችም ካለው ቅጠል በላይ ከፍ በማድረግ፣ ከእንግዲህ ራሱን በትዕቢት አያንጠራራም። ከእንግዲህ ውሃ በሚገባ ያገኘ ማንኛውም ዛፍ ወደዚህ ዐይነቱ ከፍታ አይደርስም። ሁሉም ከምድር በታች ወደ ጕድጓድ ከሚወርድ ሟች ጋራ ዐብሮ እንዲሞት ተወስኖበታልና።

15 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ መቃብር በወረደበት ቀን ጥልቅ ምንጮችን ስለ እርሱ በሐዘን ሸፈንኋቸው፤ ወንዞቹን ገታሁ፤ ታላላቅ ፈሳሾችም ተቋረጡ። በርሱም ምክንያት ሊባኖስን ጨለማ አለበስሁ፤ የደን ዛፎችም ሁሉ ደረቁ።

16 ወደ ጕድጓድ ከሚሄዱት ጋራ ወደ መቃብር ባወረድሁት ጊዜ ሲወድቅ በተሰማው ድምፅ አሕዛብ ደነገጡ። ከዚያም የዔድን ዛፎች ሁሉ፣ ምርጥና ልዩ የሆኑት የሊባኖስ ዛፎች፣ ውሃ የጠገቡትም ዛፎች ሁሉ ከምድር በታች ሆነው ተጽናኑ።

17 ከአሕዛብ መካከል ከርሱ ጋራ ያበሩ፣ በጥላው ሥር የኖሩ፣ በሰይፍ ከሞቱት ጋራ ለመቀላቀል ወደ መቃብር ወርደዋል።

18 “ ‘በዔድን ካሉት ዛፎች በውበትና በትልቅነት የሚወዳደርህ የትኛው ነው? ይሁን እንጂ አንተም እንደዚሁ ከዔድን ዛፎች ጋራ ከመሬት በታች ትወርዳለህ፤ በሰይፍ ከተገደሉት፣ ካልተገረዙትም መካከል ትጋደማለህ። “ ‘እንግዲህ ፈርዖንና ስፍር ቍጥር የሌለው ሕዝቡ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告