Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 30 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ስለ ግብጽ የወጣ ሙሾ

1 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ዋይ! በል፤ እንዲህም በል፤ “ወዮ ለዚያ ቀን!”

3 ቀኑ ቅርብ ነው፤ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፤ የደመና ቀን፣ ለአሕዛብም የጥፋት ቀን ነው።

4 በግብጽ ላይ ሰይፍ ይሆናል፤ በኢትዮጵያም ላይ ጭንቀት ይመጣል። የታረዱት በግብጽ ሲወድቁ፣ ሀብቷ ይወሰዳል፤ መሠረቶቿም ይፈርሳሉ።

5 ኢትዮጵያና ፉጥ፣ ሉድም መላው ዐረብ፣ ሊብያና የቃል ኪዳኑ ምድር ሕዝብ ከግብጽ ጋራ በአንድነት በሰይፍ ይወድቃሉ።

6 “ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘የግብጽ ተባባሪዎች ይወድቃሉ። የምትኵራራበት ብርታቷ ይወድቃል። ከሚግዶል እስከ አስዋን፣ በውስጧ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

7 በባድማ መሬቶች መካከል፣ ባድማ ይሆናሉ፤ ከተሞቻቸውም፣ ከፈራረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ።

8 በግብጽ ላይ እሳት ስጭር፣ ረዳቶቿ ሁሉ ሲደቅቁ፣ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

9 “ ‘በዚያ ቀን ከእኔ ዘንድ መልእክተኞች በመርከብ ወጥተው ያለ ሥጋት ከተቀመጠችበት ሁኔታ ለማውጣት ኢትዮጵያን ያስፈራሯታል፤ ግብጽ በጨለማ በምትዋጥበት ቀን ጭንቅ ይይዛቸዋል፤ ቀኑ በርግጥ ይመጣልና።

10 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፣ ስፍር ቍጥር የሌለውን የግብጽን ሕዝብ እደመስሳለሁ።

11 ከአሕዛብ ሁሉ እጅግ ጨካኝ የሆኑት፣ እርሱና ሰራዊቱ፣ ምድሪቱን ለማጥፋት እንዲመጡ ይደረጋል፤ ሰይፋቸውን በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ፤ ምድሪቱንም ሬሳ በሬሳ ያደርጋሉ፤

12 የአባይን ወንዝ ውሃ አደርቃለሁ፤ ምድሪቱን ለክፉ ሰዎች እሸጣለሁ፤ በባዕዳን እጅ፣ ምድሪቷንና በውስጧ ያለውን ሁሉ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።

13 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ጣዖታትን አጠፋለሁ፤ በሜምፊስ ያሉትን ምስሎች እደመስሳለሁ። ከእንግዲህ በግብጽ ገዥ አይኖርም፣ በምድሪቱም ላይ ፍርሀት እሰዳለሁ።

14 ጳትሮስን ባድማ አደርጋለሁ፤ በጣኔዎስ ላይ እሳት እለኵሳለሁ፤ በቴብስ ላይ ቅጣት አመጣለሁ።

15 የግብጽ ምሽግ በሆነችው፣ በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፤ ስፍር ቍጥር የሌለውን የቴብስን ሕዝብ አጠፋለሁ።

16 በግብጽ ላይ እሳት አነድዳለሁ፤ ሲን በጭንቅ ትናጣለች፤ ቴብስ በማዕበል ትወሰዳለች፤ ሜምፊስ በማያቋርጥ ጭንቀት ውስጥ ትገባለች።

17 የሄልዮቱ የቡባስቱ ጕልማሶች፣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ከተሞቹ ራሳቸውም ይማረካሉ።

18 የግብጽን ቀንበር በምሰብርበት ጊዜ፣ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል፤ ከዚያም የተኵራራችበት ብርታት ይንኰታኰታል። በደመና ትሸፈናለች፤ መንደሮቿም ይማረካሉ።

19 ስለዚህ በግብጽ ላይ ቅጣቴን አመጣለሁ፤ እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

20 በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር በሰባተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፤ ይፈወስ ዘንድ ክንዱ አልተጠገነም፤ ወይም ሰይፍ መያዝ ይችል ዘንድ እጁ በመቃ አልታሰረም።

22 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ተነሥቻለሁ፤ ደኅናውንና የተሰበረውን፣ ሁለቱንም ክንዶቹን እሰብራለሁ፤ ሰይፉም ከእጁ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።

23 ግብጻውያንን በሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።

24 የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፤ ሰይፌንም አስይዘዋለሁ፤ የፈርዖንን ክንድ ግን እሰብራለሁ፤ እርሱም በፊቱ ክፉኛ እንደ ቈሰለ ሰው ያቃስታል።

25 የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፤ የፈርዖን ክንድ ግን ይዝላል፤ ሰይፌን በባቢሎን ንጉሥ እጅ ሳስይዝ፣ እርሱም ሲነቀንቀው፣ ያኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።

26 በሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告