Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 28 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በጢሮስ ንጉሥ ላይ የተነገረ ትንቢት

1 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለጢሮስ ገዥ እንዲህ በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ልብህ በትዕቢት ተወጥሮ፣ “እኔ አምላክ ነኝ፤ በአምላክ ዙፋን ላይ፣ በባሕሮችም ልብ ተቀምጫለሁ” አልህ። ምንም እንኳ እንደ አምላክ ጠቢብ ነኝ ብለህ ብታስብም፣ አንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም።

3 ከዳንኤል ይልቅ ጠቢብ ነህን? ከአንተስ የተሰወረ ምስጢር የለምን?

4 በጥበብህና በማስተዋልህ፣ የራስህን ሀብት አከማቸህ፤ ወርቅም ብርም፣ በግምጃ ቤትህ አጠራቀምህ።

5 በንግድ ሥራ እጅግ ከመራቀቅህ የተነሣ፣ በሀብት ላይ ሀብት አካበትህ፤ ከሀብትህ ብዛት የተነሣም፤ ልብህ በትዕቢት ተወጠረ።

6 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘እንደ አምላክ ጥበበኛ ነኝ፤ ብለህ ስለምታስብ፣

7 ከአሕዛብ መካከል እጅግ ጨካኞች የሆኑትን ባዕዳን፣ በአንተ ላይ አመጣለሁ፤ በጥበብህ ውበት ላይ ሰይፋቸውን ይመዝዛሉ፤ ታላቅ ክብርህንም ያረክሳሉ።

8 ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፤ በጥልቁም ባሕር ውስጥ፣ በባሕሮችም ልብ ውስጥ አስከፊ ሞት ትሞታለህ።

9 ታዲያ በገዳዮችህ ፊት፣ “አምላክ ነኝ” ትላለህን? በገዳዮችህ እጅ ስትገባ፣ አንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም።

10 በባዕዳን እጅ፣ ያልተገረዙትን ሰዎች አሟሟት ትሞታለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

11 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

12 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ጢሮስ ንጉሥ ሙሾ አውርድ፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ጥበብን የተሞላህ፣ ፍጹም ውበትን የተላበስህ፣ የፍጹምነት ምሳሌ ነበርህ።

13 በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ፣ በዔድን ነበርህ፤ እያንዳንዱ የከበረ ድንጋይ አስጊጦህ ነበር፤ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮን፣ አልማዝ፣ መረግድ፣ ኢያሰጲድ፣ ሰንፔር፣ በሉር፣ ቢረሌና የከበረ ዕንቍ። ልብስህም የሚያብረቀርቅ ዕንቍ ወርቅ ነበር፤ የተዘጋጁትም አንተ በተፈጠርህበት ዕለት ነበር።

14 ጠባቂ ኪሩብ ሆነህ ተቀብተህ ነበር፤ ለዚሁም ሾምሁህ፤ በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ነበርህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ።

15 ከተፈጠርህበት ቀን ጀምሮ፣ ክፋት እስከ ተገኘብህ ድረስ፣ በመንገድህ ነቀፋ አልነበረብህም።

16 ንግድህ ስለ ደረጀ፣ በዐመፅ ተሞላህ፣ ኀጢአትም ሠራህ፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ተራራ በውርደት አሳደድሁህ፤ ጠባቂ ኪሩብ ሆይ፤ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አስወጣሁህ።

17 በውበትህ ምክንያት፣ ልብህ ታበየ፤ ከክብርህ ታላቅነት የተነሣም፣ ጥበብህን አረከስህ። ስለዚህ ወደ ምድር ወረወርሁህ፤ ለነገሥታት ትዕይንት አደረግሁህ።

18 በኀጢአትህና በተጭበረበረው ንግድህ ብዛት፣ መቅደስህን አረከስህ። ስለዚህ እሳት ከአንተ እንዲወጣ አደረግሁ፤ እርሱም በላህ፤ በሚመለከቱህ ሁሉ ፊት፣ በምድር ላይ ዐመድ አደረግሁህ።

19 የሚያውቁህን አሕዛብ ሁሉ፣ ሁኔታህ አስደንግጧቸዋል፤ መጨረሻህ የሚያሳዝን ሆነ፤ ከእንግዲህ ህልውና የለህም።’ ”


በሲዶን ላይ የተነገረ ትንቢት

20 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ሲዶና አዙር፤ ትንቢትም ተናገርባት፤

22 እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ሲዶን ሆይ፤ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በውስጥሽ እከብራለሁ፤ ቅጣትን ሳመጣባት፣ ቅድስናዬንም በውስጧ ስገልጥ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

23 በርሷ ላይ መቅሠፍት አመጣለሁ፤ በመንገዶቿ ላይ ደም እንዲፈስስ አደርጋለሁ፤ ከየአቅጣጫው በሚመጣ ሰይፍ፣ የታረዱት በውስጧ ይወድቃሉ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

24 “ ‘ከእንግዲህ ወዲያ የእስራኤል ሕዝብ የሚያሠቃይ አሜከላና የሚወጋ እሾኽ የሆኑ ጎረቤቶች አይኖሯቸውም፤ ከዚያም እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

25 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤልን ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች መካከል በምሰበስብበት ጊዜ፣ አሕዛብ እያዩ ቅድስናዬን በመካከላቸው እገልጣለሁ፤ ከዚያም በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ፤ ይህም ለባሪያዬ ለያዕቆብ የሰጠሁት ነው።

26 በዚያም ያለ ሥጋት ይኖራሉ፤ ቤቶች ይሠራሉ፤ የወይን ተክል ቦታም ያበጃሉ። ያጣጣሏቸው ጎረቤቶቻቸውን ሁሉ በምቀጣበት ጊዜ እነርሱ በሰላም ይኖራሉ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告