Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 26 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት

1 በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ! ጢሮስ ስለ ኢየሩሳሌም፣ ‘ዕሠይ! የሕዝቦች በር ተሰበረች፤ ደጆቿም ወለል ብለው ተከፈቱልኝ፤ እንግዲህ እርሷ ስለ ፈራረሰች እኔ እከብራለሁ’ ብላለችና፤

3 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ጢሮስ ሆይ፤ እነሆ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ባሕር ሞገዷን እንደምታስነሣ፣ ብዙ ሕዝብ አስነሣብሻለሁ።

4 የጢሮስን ቅጥሮች ያወድማሉ፤ ምሽጎቿንም ያፈርሳሉ። ዐፈሯን ከላይዋ ጠርጌ የተራቈተ ዐለት አደርጋታለሁ።

5 እኔ ጌታ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፤ በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆናለች፤ አሕዛብም ይበዘብዟታል፤

6 መኻል አገር ያሉ ሰፈሮቿም በሰይፍ ይወድማሉ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’

7 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ከፈረሶችና ከሠረገሎች ጋራ፣ ከፈረሰኞችና ከታላቅ ሰራዊትም ጋራ ከሰሜን በጢሮስ ላይ አመጣለሁ።

8 እርሱ መኻል አገር ያሉ ሰፈሮችሽን በሰይፍ ያወድማቸዋል፤ በዙሪያሽ ካብ ይክባል፤ እስከ ቅጥሮችሽ ጫፍ ድረስ ዐፈር ይደለድልብሻል፤ ጋሻውንም በአንቺ ላይ ያነሣል።

9 ግንብ መደርመሻውን በቅጥሮቿ ላይ ያነጣጥራል፤ በመሣሪያም ምሽጎችሽን ያፈርሳል።

10 ከፈረሶቹ ብዛት የተነሣ ዐቧራ ይሸፍንሻል፤ ሰዎች ቅጥሮቿ ወደ ፈረሱ ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ በሚገባበት ጊዜ፣ ከፈረሶቹና ከጋሪዎቹ፣ ከሠረገሎቹም ድምፅ የተነሣ ቅጥሮችሽ ይናወጣሉ።

11 መንገዶችሽ ሁሉ በፈረሶቹ ኰቴ ይረጋገጣሉ፤ ሕዝብሽን በሰይፍ ይገድላል፤ ታላላቅ ምሰሶዎችሽ ወደ ምድር ይወድቃሉ።

12 ሀብትሽን ይዘርፋሉ፤ ሸቀጥሽን ይበዘብዛሉ፤ ቅጥሮችሽን ያፈርሳሉ፤ የተዋቡ ቤቶችሽን ያወድማሉ፤ ድንጋይሽን፣ ዕንጨትሽንና የግንቦች ፍርስራሽ ወደ ባሕር ይጥላሉ።

13 ዘፈንሽን ጸጥ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም የበገናሽ ድምፅ አይሰማም።

14 የተራቈተ ዐለት አደርግሻለሁ፤ የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆኛለሽ፤ እንደ ገናም ተመልሰሽ አትሠሪም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

15 “ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላል፤ ‘የቈሰሉት ሲያቃስቱ፣ በውስጥሽም ጭፍጨፋ ሲካሄድ፣ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች አይነዋወጡምን?

16 የባሕር ጠረፍ መሳፍንት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ይጥላሉ፤ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውን ያወልቃሉ። ፍርሀት ተከናንበው በመሬት ላይ በመቀመጥ ባለማቋረጥ፣ እየተንቀጠቀጡ በአንቺ ላይ በደረሰው ነገር ይሸበራሉ፤’

17 ስለ አንቺም እንዲህ ብለው ሙሾ ያወርዳሉ፤ “ ‘በባሕር ሰዎች የሚኖሩብሽ፣ ባለዝናዋ ከተማ ሆይ፤ እንዴት ጠፋሽ! ከነዋሪዎችሽ ጋራ፣ የባሕር ላይ ኀያል ነበርሽ፤ በዚያ በሚኖሩትም ሁሉ ዘንድ የተፈራሽ ነበርሽ።

18 አሁን በመውደቂያሽ ቀን፣ በጠረፍ ያሉ አገሮች ተናወጡ፤ ከመፍረስሽም የተነሣ፤ በባሕር ውስጥ ያሉ ደሴቶች ተደናገጡ።’

19 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች ባድማ ሳደርግሽ፣ የውቅያኖስንም ውሃ በላይሽ አድርጌ በቀላይ ስሸፍንሽ፣

20 የጥንት ዘመን ሰዎች ወደ ገቡበት ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋራ አወርድሻለሁ፤ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋራ በጥንቱ ፍርስራሽ ከምድር በታች አኖርሻለሁ፤ ከዚህም በኋላ በሕያዋን ምድር ተመልሰሽ ቦታ አታገኚም፤

21 መጨረሻሽን አሳዛኝ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊያለሽ፤ ከቶም አትገኚም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告