Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 25 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በአሞን ላይ የተነገረ ትንቢት

1 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ አሞናውያን አድርገህ፣ ትንቢት ተናገርባቸው፤

3 ለአሞንም ልጆች እንዲህ በላቸው፤ ‘የጌታ፣ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መቅደሴ በረከሰ ጊዜ፣ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ፣ የይሁዳም ቤት ተማርኮ በተወሰደ ጊዜ፣ “ዕሠይ!” ብላችኋልና፣

4 ለምሥራቅ ሕዝብ ትገዙ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በመካከላችሁ ይሰፍራሉ፤ ድንኳኖቻቸውንም በዚያ ይተክላሉ፤ ፍሬያችሁን ይበላሉ፤ ወተታችሁንም ይጠጣሉ።

5 የረባት ከተማ የግመሎች መሰማሪያ፣ አሞንንም የበጎች መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

6 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ በልባችሁ ክፋት ሁሉ፣ በእስራኤል ውድቀት ላይ በመደሰት በእጃችሁ አጨብጭባችኋልና፤ በመዝለልም ጨፍራችኋልና

7 ክንዴን በእናንተ ላይ አነሣለሁ፤ በአሕዛብ እንድትበዘበዙ አደርጋለሁ፤ ከሕዝቦች መካከል አውጥቼ፣ ከአገሮችም ለይቼ አጠፋችኋለሁ፤ እደመስሳችኋለሁም። በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”


በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት

8 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሞዓብና ሴይር፣ “እነሆ የይሁዳ ቤት እንደ ሌሎቹ አሕዛብ ሁሉ ሆነ” ብለዋልና፤

9 በምድሪቱ ድንበር ላይ ካሉትና ክብሯ ከሆኑት ከተሞች ከቤትየሺሞት፣ ከበኣልሜዎንና ከቂርያታይም ጀምሬ የሞዓብን ዐምባ እገልጣለሁ።

10 ሞዓባውያንንም ከአሞናውያን ጋራ ይገዙላቸው ዘንድ፣ ለምሥራቅ ሕዝብ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አሞናውያን በአሕዛብ ዘንድ ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖራቸውም።

11 ሞዓብንም እቀጣለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”


በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት

12 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ኤዶም የይሁዳን ቤት ተበቅሏልና፤ በዚህም በደለኛ ሆኗልና፤

13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ክንዴን በኤዶም ላይ አነሣለሁ፤ ሰዎቹንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ፤ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከቴማንም ጀምሮ እስከ ድዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ።

14 በሕዝቤ በእስራኤል አማካይነት ኤዶምን እበቀላለሁ፤ እነርሱም እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴ መጠን በኤዶም ሕዝብ ላይ ያደርጋሉ፤ ኤዶማውያንም በቀሌን ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”


በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት

15 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ፍልስጥኤማውያን በቂም ተነሣሥተው በክፉ ልብ ተበቅለዋልና፣ ይሁዳንም በቈየ ጠላትነት ለማጥፋት ፈልገዋልና፤

16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ክንዴን በፍልስጥኤማውያን ላይ አነሣለሁ፤ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፤ በባሕሩ ጠረፍ ላይ የቀሩትንም አጠፋለሁ።

17 በታላቅ በቀል እበቀላቸዋለሁ፤ በመዓቴም እቀጣቸዋለሁ፤” በምበቀላቸውም ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告