Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 24 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የድስቱ ምሳሌ

1 በዘጠነኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን ቀን፣ የዛሬውን ዕለት፣ ለይተህ መዝግብ፤ የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በዚህ ቀን ከብቧታልና።

3 ለዚህ ዐመፀኛ ቤት እንዲህ ብለህ ተምሳሌት ተናገር፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ብረት ድስት በእሳት ላይ ጣድ፤ ከጣድህም በኋላ ውሃ ጨምርበት።

4 ሙዳ፣ ሙዳ ሥጋ፣ ምርጥ ምርጡን ቍርጥ ሁሉ፣ ጭንና ወርቹን ጨምርበት፤ የተመረጡ ዐጥንቶችንም ሙላበት።

5 ከመንጋው ሙክቱን ውሰድ፤ ዐጥንቱን ለማብሰል ብዙ ማገዶ ከሥሩ ጨምር፤ ሙክክ እስከሚል ቀቅለው፤ ዐጥንቱም ይብሰል።

6 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “ ‘ለዛገችው ብረት ድስት ዝገቷም ለማይለቅ፣ ደም ላፈሰሰችው ከተማ ወዮላት! መለያ ዕጣ ሳትጥል አንድ በአንድ አውጥተህ ባዶ አድርገው።

7 “ ‘የሰው ደም በመካከሏ አለ፤ በገላጣ ዐለት ላይ አደረገችው እንጂ፣ ዐፈር ሊሸፍነው በሚችል፣ በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም።

8 ቍጣዬ እንዲነድድና ለመበቀል እንዲያመቸኝ፣ ይሸፈንም ዘንድ እንዳይችል፣ ደሟን በገላጣ ዐለት ላይ አፈሰስሁ።

9 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ደም ላፈሰሰችው ከተማ ወዮላት! እኔም ደግሞ የምትቃጠልበትን ማገዶ እቈልላለሁ።

10 ማገዶውን ከምርበት፤ እሳቱን አንድድ፤ ቅመም ጨምረህበት፣ ሥጋውን በሚገባ ቀቅል፤ ዐጥንቱም ይረር።

11 ጕድፉ እንዲቀልጥ፣ ዝገቱም በእሳት እንዲበላ፣ ባዶው ድስት እስኪሞቅ፣ መደቡም እስኪግል ከሰል ላይ ጣደው።

12 ብዙ ጕልበት ቢፈስስበትም፣ የዝገቱ ክምር፣ በእሳት እንኳ፣ ሊለቅ አልቻለም።

13 “ ‘የረከስሽው በብልግናሽ ነው፤ ቍጣዬ በአንቺ ላይ እስኪፈጸም ድረስ ከእንግዲህ ንጹሕ አትሆኚም፤ ከርኩሰትሽ ላነጻሽ ፈልጌ፣ መንጻት አልወደድሽምና።

14 “ ‘እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ የምሠራበትም ጊዜ ደርሷል፤ ወደ ኋላ አልልም፤ አልራራም፤ አላመነታምም። እንደ መንገድሽና እንደ ተግባርሽ ይፈረድብሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”


የሕዝቅኤል ሚስት መሞት

15 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

16 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የዐይንህ ማረፊያ የሆነውን ነገር በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተ ግን ዋይታ አታሰማ፤ አታልቅስ፤ እንባህንም አታፍስስ፤

17 ድምፅህን ዝቅ አድርገህ በሐዘን አንጐራጕር እንጂ ለሞተው አታልቅስ። ጥምጥምህን ከራስህ አታውርድ፤ ጫማህንም አታውልቅ፤ አፍህ ድረስ አትሸፋፈን፤ የዕዝን እንጀራም አትብላ።”

18 እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፤ ሚስቴም ማታውኑ ሞተች፤ በማግስቱም ጧት እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።

19 ሕዝቡም፣ “ይህን ስታደርግ ለእኛ የምታስተላልፈው መልእክት ምን እንደ ሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ።

20 እኔም እንዲህ አልኋቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

21 ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የኀይላችሁን ትምክሕት፣ የዐይናችሁ ማረፊያና የልባችሁ ደስታ የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ። ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንድና ሴት ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።

22 እኔ እንዳደረግሁም ታደርጋላችሁ፤ አፋችሁ ድረስ አትሸፋፈኑም፤ የዕዝን እንጀራም አትበሉም፤

23 ጥምጥማችሁን ከራሳችሁ አታወርዱም፤ ጫማችሁንም አታወልቁም። በኀጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፤ እርስ በርስ ታቃስታላችሁ እንጂ ሐዘን አትቀመጡም፤ አታለቅሱምም።

24 ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገው ታደርጋላችሁ፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’

25 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፤ ኀይላቸውን፣ ደስታቸውንና፣ ክብራቸውን፣ የዐይናቸው ማረፊያና የልባቸው ደስታ የሆኑትን ወንድና ሴት ልጆቻቸውን ጭምር በምወስድባቸው ቀን፣

26 በዚያ ቀን፣ ያመለጠ ሰው ይህን ወሬ ሊነግርህ ወደ አንተ ይመጣል፤

27 በዚያ ቀን አፍህ ተከፍቶ ከርሱ ጋራ ትነጋገራለህ፤ ከዚያም በኋላ እንደ ድዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告