Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የቅጣት በትር የሆነችው ባቢሎን

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አዙር፤ በመቅደሱ ላይ ቃል ተናገር፤ በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተንብይ፤

3 እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ሰይፌን ከሰገባው እመዝዛለሁ፤ ጻድቁንም፣ ክፉውንም ከአንተ ዘንድ አስወግዳለሁ።

4 ጻድቁንም ክፉውንም ስለማስወግድ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ባለው ሕዝብ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል።

5 ሰይፌን ከሰገባው የመዘዝሁት እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ሕዝቡ ሁሉ ያውቃል፤ እርሱም ወደ ሰገባው አይመለስም።’

6 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ አቃስት! በተሰበረ ልብና በመረረ ሐዘን አቃስት፤

7 እነርሱም፣ ‘ለምን ታቃስታለህ?’ ቢሉህ፣ ‘ስለሚመጣው ክፉ ወሬ ነው፤ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፤ እጅም ሁሉ ይዝላል፤ ነፍስ ሁሉ ይደክማል፤ ጕልበትም ሁሉ ውሃ ይሆናል’ በላቸው። እነሆ፤ ይመጣል፤ ይፈጸማልም ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

8 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

9 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፤ “ ‘ሰይፍ! ሰይፍ! የተሳለ የተወለወለም፤

10 የተሳለው ሊገድል፣ የተወለወለውም እንደ መብረቅ ሊብረቀረቅ ነው! “ ‘ታዲያ፣ እንዴት ደስ ሊለን ይችላል? ሰይፉ የልጄን በትረ መንግሥት እንደ ማንኛውም በትር ንቋል።

11 “ ‘በእጁ እንዲያዝ፣ ሰይፉ ሊወለወል ተሰጥቷል፤ ገዳዩ በእጁ እንዲጨብጠው፣ ተስሏል፤ ተወልውሏል።

12 የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ በሕዝቤ ላይ፣ በእስራኤልም መሳፍንት ሁሉ ላይ መጥቷልና፤ ጩኸት፣ ዋይታም አሰማ። እነርሱ ከሕዝቤ ጋራ በአንድ ላይ፣ ለሰይፍ ተጥለዋል፤ ስለዚህ ደረትህን ምታ።

13 “ ‘ፈተና በርግጥ ይመጣል፤ ሰይፉ የናቀው በትረ መንግሥት ዘላቂነት ባይኖረውስ? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

14 “እንግዲህ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ በእጅህም አጨብጭብ፤ ሰይፉ ሁለት ጊዜ፣ ሦስት ጊዜም ይምታ፤ በእጅጉ የሚገድል፣ ለግድያ የሚሆን፣ በየአቅጣጫውም የሚከባቸው ሰይፍ ነው።

15 ልብ ሁሉ ይቀልጥ ዘንድ፣ የሚወድቁትም እንዲበዙ፣ በበሮቻቸው ሁሉ፣ የግድያውን ሰይፍ አኑሬአለሁ። ወዮ! እንዲያብረቀርቅ ተወልውሏል፤ ለመግደልም ተመዝዟል።

16 ሰይፍ ሆይ፤ በስለትህ አቅጣጫ ሁሉ፣ ወደ ቀኝም፣ ወደ ግራም ቍረጥ።

17 እኔም በእጄ አጨበጭባለሁ፤ ቍጣዬም ይበርዳል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”

18 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

19 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የሚመጣባቸውን የሁለት መንገዶች ካርታ ንደፍ፤ መንገዶቹም ከአንድ አገር የሚነሡ ናቸው፤ መንገዱ ወደ ከተማው በሚገነጠልበት ቦታ ላይ ምልክት አቁም።

20 በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ ለሚመጣው ሰይፍ አንደኛውን መንገድ ምልክት አድርግ፤ በይሁዳና በተመሸገችው ከተማ በኢየሩሳሌም ላይ ለሚመጣውም ሰይፍ ሁለተኛውን መንገድ ምልክት አድርግ።

21 የባቢሎን ንጉሥ በጥንቈላ ምሪት ለማግኘት በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ ጐዳናዎች መጋጠሚያ ላይ ይቆማል፤ ቀስቶቹን በመወዝወዝ ዕጣ ይጥላል፤ አማልክቱን ያማክራል፤ ጕበትንም ይመረምራል።

22 የቅጥር መደርመሻ አምጥቶ እንዲያቆም፣ ለመግደል ትእዛዝ እንዲሰጥ፣ ፉከራ እንዲያሰማ፣ ቅጥር መደርመሻውን በከተሞች በር ላይ እንዲያደርግ፣ የዐፈር ድልድል እንዲያበጅና ምሽግ እንዲሠራ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ወጣ።

23 ይህም ከርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ለገቡት የተሳሳተ የጥንቈላ ምሪት ይመስላል፤ እርሱ ግን በደላቸውን ያሳስባቸዋል፤ ማርኮም ይዟቸው ይሄዳል።

24 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ በምታደርጉት ሁሉ ኀጢአታችሁን በመግለጽ፣ በግልጽም በማመፅ በደላችሁን ስላሳሰባችሁ፣ እንዲህም ስላደረጋችሁ በምርኮ ትወሰዳላችሁ።

25 “ ‘አንተ የግፍ ጽዋህ የሞላ፣ የምትቀጣበት ቀን የደረሰ፣ ርኩስና ክፉ የእስራኤል መስፍን ሆይ፤

26 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ እንደ ከዚህ በፊቱ አይሆንም፤ ዝቅ ያለው ከፍ ይላል፤ ከፍ ያለውም ዝቅ ይላል።

27 ባድማ! ባድማ! ባድማ አደርጋታለሁ፤ የሚገባው ባለመብት እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ።” ’

28 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ስለ አሞናውያንና ስለ ስድባቸው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ሰይፍ! ሰይፍ! ሊገድል የተመዘዘ፣ ሊያጠፋ የተጠረገ፣ እንደ መብረቅ ሊያብረቀርቅ የተወለወለ፤

29 የታለመልህ የሐሰት ራእይ፣ የተነገረልህ የውሸት ሟርት ቢኖርም፣ የግፍ ጽዋቸው በሞላ፣ ቀናቸው በደረሰ፣ መታረድ በሚገባቸው ክፉዎች፣ ዐንገት ላይ ይሆናል።

30 “ ‘ሰይፉን ወደ ሰገባው መልሰው፤ በተፈጠርህበት ምድር፣ በተወለድህበትም አገር፣ በዚያ እፈርድብሃለሁ።

31 መዓቴን በላይህ አፈስሳለሁ፤ የቍጣዬንም እሳት አነድድብሃለሁ፣ በጥፋት ለተካኑ፣ ለጨካኞች ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

32 ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፣ ደምህ በምድርህ ይፈስሳል፣ ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖርህም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告