Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ዐመፀኛዪቱ እስራኤል

1 በሰባተኛው ዓመት፣ በዐምስተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊጠይቁ መጡ፤ በፊቴም ተቀመጡ።

2 ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

3 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሐሳቤን ልትጠይቁ መጣችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ ከእኔ ጠይቃችሁ እንድትረዱ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

4 “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህን ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? በውኑ ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? የቀድሞ አባቶቻቸውን አስጸያፊ ተግባር ግለጥላቸው፤

5 እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፣ ለያዕቆብ ቤት ዘር እጄን አንሥቼ ማልሁላቸው፤ በግብጽም ራሴን ገለጥሁላቸው። እጄንም አንሥቼ፣ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው።”

6 በዚያ ቀን፣ ከግብጽ አውጥቻቸው ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወዳዘጋጀሁላቸውም ምድር እንደማስገባቸው ማልሁላቸው።

7 እኔም፣ “እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብጽ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” አልኋቸው።

8 “ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብጽንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብጽ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር።

9 ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብጽ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ።

10 ስለዚህ ከግብጽ አውጥቼ ወደ ምድረ በዳ አመጣኋቸው።

11 ሰው ቢጠብቀው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን ሰጠኋቸው፤ ሕጌንም አስታወቅኋቸው።

12 ደግሞም እኔ እግዚአብሔር እንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው።

13 “ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር።

14 ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ።

15 ደግሞም ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወደ ሰጠኋቸውም ምድር እንደማላስገባቸው እጆቼን አንሥቼ በምድረ በዳ በፊታቸው ማልሁ፤

16 ምክንያቱም ሕጎቼን ተላልፈዋል፤ ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሰንበቴንም አርክሰዋል፤ ልባቸው ከጣዖቶቻቸው ጋራ ተጣብቋልና።

17 እኔ ግን በርኅራኄ ተመለከትኋቸው እንጂ አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም አልፈጀኋቸውም።

18 ለልጆቻቸው በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፤ “የአባቶቻችሁን ሥርዐት አትከተሉ፤ ወጋቸውን አትጠብቁ፤ ራሳችሁንም በጣዖቶቻቸው አታርክሱ።

19 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዐቴን ተከተሉ፤ ሕጌንም ለመጠበቅ ትጉ።

20 በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆን ዘንድ ሰንበቴን የተቀደሰ ቀን አድርጉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁም ታውቃላችሁ።”

21 “ ‘ልጆቻቸው ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልተከተሉም፤ ሕጌን ለመጠበቅ አልተጉም፤ ሰንበቴንም አረከሱ። እኔም በምድረ በዳ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም አወርድባቸዋለሁ ብዬ ነበር።

22 ነገር ግን ከግብጽ ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ እጄን ሰበሰብሁ።

23 ደግሞም በአሕዛብ መካከል እንደምበትናቸውና ወደ ተለያዩ አገሮች እንደማፈልሳቸው በምድረ በዳ እጄን አንሥቼ በፊታቸው ማልሁ፤

24 ምክንያቱም ሥርዐቴን አቃለሉ፤ ሰንበቴን አረከሱ እንጂ ሕጌን አልጠበቁም፤ ዐይናቸውም ከአባቶቻቸው ጣዖታት ጋራ ተጣብቋል።

25 እኔም መልካም ላልሆነ ሥርዐትና በሕይወት ለማይኖሩበት ሕግ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤

26 እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ፣ አስደነግጣቸውም ዘንድ በእሳት በሚያቀርቡት የበኵር ልጅ መሥዋዕት እንዲረክሱ አደረግኋቸው።’

27 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አባቶቻችሁ ታማኝነታቸውን በማጕደላቸው በዚህ ደግሞ አቃለሉኝ፤

28 ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር ባስገባኋቸው ጊዜ፣ ከፍ ያለውን ኰረብታ ሁሉና የለመለመውን ዛፍ ሁሉ ተመለከቱ፤ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ፤ ቍርባናቸውን በማቅረብ ቍጣዬን አነሣሡ፤ መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣናቸውን ዐጠኑ፤ የመጠጥ ቍርባናቸውንም አፈሰሱ።

29 እኔም፣ የምትሄዱበት ይህ ከፍታ ቦታ ምንድን ነው?’ ” አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ይጠራል።


ቅጣትና ምሕረት

30 “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አባቶቻችሁ እንዳደረጉት ራሳችሁን ታረክሳላችሁን? በረከሱ ምስሎቻቸው ምኞት ትቃጠላላችሁን?

31 ቍርባናችሁን በምታቀርቡበት ጊዜ ልጆቻችሁን ለእሳት በመዳረግ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ሁሉ እየረከሳችሁ ናችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ታዲያ የእኔን ሐሳብ እንድትጠይቁ ልፍቀድላችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ እንድትጠይቁኝ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

32 “ ‘እናንተም፣ “ለዕንጨትና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ እንደ አሕዛብ፣ በዓለምም እንደሚኖረው ሕዝብ ሁሉ እንሁን” አላችሁ፤ ነገር ግን በልባችሁ ያሰባችሁት ከቶ አይሆንላችሁም።

33 በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ መዓትንም በማፍሰስ በላያችሁ እነግሣለሁ።

34 ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ፣ መዓትንም በማፍሰስ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች ሁሉ እሰበስባችኋለሁ።

35 ወደ አሕዛብ ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋራ እፋረዳለሁ።

36 በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋራ እንደ ተፋረድሁ፣ ከእናንተም ጋራ እፋረዳለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

37 ከበትሬ በታች አሳልፋችኋለሁ፤ ከቃል ኪዳኔም ጋራ አጣብቃችኋለሁ።

38 በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

39 “ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የማትሰሙኝ ከሆነ፣ እያንዳንዳችሁ ሂዱና ለጣዖቶቻችሁ ስገዱ! ነገር ግን በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን ከእንግዲህ አታረክሱም።

40 በቅዱሱ ተራራዬ፣ ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ በዚያ ምድር የእስራኤል ቤት ሁሉ ያመልከኛልና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እኔም በዚያ እቀበላቸዋለሁ። ቍርባናችሁንና በኵራታችሁን ከተቀደሱ መሥዋዕቶቻችሁ ሁሉ ጋራ በዚያ እሻለሁ።

41 ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።

42 ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

43 በዚያም መንገዳችሁንና ራሳችሁን ያረከሳችሁበትን ተግባር ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በፈጸማችሁትም ክፋት ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።

44 የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ብልሹ ተግባራችሁ ሳይሆን፣ ስለ ስሜ ስል በምጐበኛችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”


በደቡቡ አገር ላይ የተነገረ ትንቢት

45 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

46 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ደቡብ አዙር፤ በደቡብ ላይ ቃል ተናገር፤ በደቡብ አገር ደን ላይም ትንቢት ተንብይ።

47 ለደቡቡ ደን እንዲህ በል፤ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በአንተ ላይ እሳት ልለኵስ ነው፤ እሳቱ የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍህን ሁሉ ይበላል፤ የሚንቦገቦገው ነበልባሉም አይጠፋም፤ ከደቡብ እስከ ሰሜን ያለውን ፊት ሁሉ ይለበልባል።

48 ሰው ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንዳነደድሁት ያያል፤ የሚያጠፋውም የለም።’ ”

49 እኔም፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ፣ ‘ተምሳሌት ብቻ ይመስላል’ ይሉኛል” አልሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告