ሕዝቅኤል 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየሕዝቅኤል መጠራት 1 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ በእግርህ ቁም፤ እኔም እናገርሃለሁ” አለኝ። 2 እርሱም ሲናገር፣ መንፈስ ወደ ውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ ሲናገረኝም ሰማሁት። 3 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእኔ ላይ ወደ ዐመፀው፣ ወደ ዐመፀኞቹ የእስራኤል ልጆች እልክሃለሁ፤ እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐምፀውብኛል። 4 ሕዝቡም እልኸኛና ዐንገተ ደንዳና ነው፤ እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ በላቸው። 5 እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለ ሆኑ፤ ቢሰሙም ባይሰሙም በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበር ያውቃሉ። 6 አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ እነርሱን ወይም ቃላቸውን አትፍራ፤ ኵርንችትና እሾኽ በዙሪያህ ቢኖሩም፣ በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም አትፍራ። እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም፣ አንተ በሚሉህ ነገር አትፍራ፤ እነርሱም አያስደንግጡህ። 7 እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለ ሆኑ፣ ቢሰሙም ባይሰሙም አንተ ቃሌን ንገራቸው። 8 አንተ ግን የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምልህን ስማ፤ እንደዚያ ዐመፀኛ ቤት ዐታምፅ፤ አፍህን ክፈት፤ የምሰጥህንም ብላ።” 9 ከዚህም በኋላ፣ እነሆ አንድ እጅ ወደ እኔ ተዘርግቶ አየሁ፤ ጥቅልል መጽሐፍም ነበረበት፤ 10 እርሱም በፊቴ ዘረጋው፤ መጽሐፉም ከፊትና ከኋላው የሰቈቃ፣ የልቅሶና የዋይታ ቃላት ተጽፎበት ነበር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.