ሕዝቅኤል 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየማይረባው የወይን ግንድ 1 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የወይን ግንድ በዱር ካሉት ዛፎች ሁሉ ቅርንጫፍ የሚሻለው በምንድን ነው? 3 የሚጠቅም ነገር ለመሥራት ከግንዱ አንዳች ተወስዶ ያውቃልን? ዕቃ የሚንጠለጠልበትስ ኵላብ ከርሱ ይበጃልን? 4 እንዲነድድ እሳት ላይ ከተጣለ በኋላ፣ እሳቱ ጫፍና ጫፉን አቃጥሎ፣ መኻሉን ከለበለበው፣ ለአንዳች ነገር ይጠቅማልን? 5 እንግዲህ ሙሉ ሆኖ ሳለ ለምንም ነገር ካልጠቀመ፣ እሳት ካቃጠለውና ከለበለበው በኋላ ረብ የለሽነቱ የቱን ያህል የባሰ ይሆን! 6 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከዱር ዛፎች መካከል የወይን ግንድ እንዲነድድ ለእሳት አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፣ እንዲሁ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አሳልፌ እሰጣለሁ። 7 ፊቴን በክፋት ወደ እነርሱ እመልሳለሁ፤ ከእሳት ቢያመልጡም፣ ገና እሳት ይበላቸዋል። ፊቴን በክፋት ወደ እነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8 ታማኝነትን ከማጕደላቸው የተነሣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.