Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ባዕድ አምልኮ ተከታዮች መወገዛቸው

1 ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።

2 ከዚያም የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

3 “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን?

4 ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ።

5 በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’

6 “ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ!

7 “ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴ እግዚአብሔር እመልስለታለሁ።

8 ፊቴን በክፋት ወደዚያ ሰው እመልሳለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

9 “ ‘ነቢዩ ትንቢት ይናገር ዘንድ ቢታለል፣ ያን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ክንዴን በርሱ ላይ አነሣለሁ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል መካከልም አጠፋዋለሁ።

10 በደላቸው በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ነቢዩም እርሱን ሊጠይቀው ከመጣው ሰው ጋራ እኩል በደለኛ ይሆናል።

11 ከእንግዲህ የእስራኤል ሕዝብ መንገድ ስቶ ከእኔ አይለይም፤ ተመልሶም በኀጢአቱ ሁሉ ራሱን አያረክስም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”


የማያመልጡት ፍርድ

12 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

13 “የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ አገር በእኔ ባለ መታመን ቢበድለኝና እኔም እጄን በላዩ ዘርግቼ የምግብ ምንጩን ባደርቅ፣ ራብንም አምጥቼበት ሰውንና እንስሳቱን ብገድል፣

14 ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ እነዚህ ሦስቱ በዚያ ቢኖሩ እንኳ፣ በጽድቃቸው የሚያድኑት ራሳቸውን ብቻ ነው፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15 “የዱር አራዊትንም በአገሪቱ ላይ ሰድጄ፣ አገሪቱን ሕፃናት አልባ ቢያደርጓትና ከአራዊቱም የተነሣ ምድሪቱ ሰው እስከማያልፍባት ባድማ ብትሆን፣

16 ‘በሕያውነቴ እምላለሁ!’ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ቢኖሩባት እንኳ፣ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም፤ እነርሱ ብቻ ይድናሉ፤ ምድሪቱ ግን ባድማ ትሆናለች።

17 “ሰይፍን በአገሪቱ ላይ አምጥቼ፣ ‘ሰይፍ በዚህ ምድር ይለፍ’ ብል፣ ሰውንና እንስሳን ባጠፋ፣

18 በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባትም እንኳ ራሳቸው ብቻ ይድናሉ እንጂ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም።

19 “ቸነፈርንም በምድሪቱ ላይ ብሰድድና ደም በማፍሰስ መዓቴን አውርጄ ሰውንና እንስሳን ባጠፋ፣

20 በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ቢኖሩባትም እንኳ፣ በጽድቃቸው ራሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችን ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም።

21 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ሰውንና እንስሳቱን ለማጥፋት አራቱን አስፈሪ ፍርዶቼን፦ ሰይፍን፣ ራብን፣ የዱር አራዊትንና ቸነፈርን በኢየሩሳሌም ላይ በማመጣበት ጊዜ ምንኛ የከፋ ይሆን!

22 ነገር ግን ከዚያ ወጥተው የሚተርፉ ወንዶችና ሴቶች ልጆች አሉ፤ እነርሱም ወደ እናንተ ይመጣሉ፤ እናንተም አካሄዳቸውንና ተግባራቸውን በምታዩበት ጊዜ፣ በኢየሩሳሌም ላይ ስላመጣሁት መከራ፣ ስላደረስሁባትም አስከፊ ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ።

23 አካሄዳቸውንና ተግባራቸውን በምታዩበት ጊዜ፣ ትጽናናላችሁ፤ አንዳች ነገር በከንቱ እንዳላደረገሁ ትረዳላችሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告