Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደሱ ተለየ

1 እኔም አየሁ፤ እነሆ ከኪሩቤል ራስ በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ፣ የሰንፔር ዙፋን የሚመስል ነገር ነበረ።

2 እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “በኪሩቤል ሥር ወዳሉት መንኰራኵሮች መካከል ግባ፤ በኪሩቤል መካከል ካለውም የእሳት ፍም እጅህን ሞልተህ ዝገን፤ በከተማዪቱም ላይ በትነው” አለው። ሰውየውም እያየሁት ገባ።

3 ሰውየው ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ፣ ኪሩቤል በቤተ መቅደሱ ውስጥ በደቡብ በኩል ቆመው ነበር፤ ደመናም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላ።

4 የእግዚአብሔርም ክብር ከነበረበት ከኪሩቤል በላይ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መድረክ ሄደ፤ ደመናው ቤተ መቅደሱን ሞላ፤ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ተሞላ።

5 ሁሉን ቻይ አምላክ ሲናገር እንደሚሰማው ድምፅ ዐይነት፣ የኪሩቤል ክንፎች ድምፅ እስከ ውጪው አደባባይ ድረስ ይሰማ ነበር።

6 እግዚአብሔር በፍታ የለበሰውን ሰው፣ “ከኪሩቤል ዘንድ ከመንኰራኵሮቹ መካከል እሳት ውሰድ” ብሎ ባዘዘው ጊዜ፣ ሰውየው ወደ ውስጥ ገብቶ በአንዱ መንኰራኵር አጠገብ ቆመ።

7 ከኪሩቤልም አንዱ በመካከላቸው ወዳለው እሳት እጁን ዘርግቶ ጥቂት ወሰደ፤ በፍታ በለበሰው ሰው እጅ ላይ አኖረው፤ እርሱም ይዞ ወጣ።

8 ከኪሩቤል ክንፎች ሥር የሰው እጅ የሚመስል ይታይ ነበር።

9 እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፤ በእያንዳንዱ ኪሩብ አጠገብ አንድ መንኰራኵር ነበር፤ የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌ ያንጸባርቅ ነበር።

10 የአራቱም መልክ ይመሳሰል ነበር፤ እያንዳንዱም መንኰራኵር በመንኰራኵር ውስጥ ተሰክቶ የተሠራ ይመስል ነበር።

11 መንኰራኵሮቹ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜም ኪሩቤል ወደ ዞሩበት ወደ አራቱ አቅጣጫ ሁሉ መሄድ ይችሉ ነበር፤ ኪሩቤል በሚሄዱበት ጊዜ መንኰራኵሮቹ ወዲያ ወዲህ አይሉም ነበር፤ ኪሩቤል በሚሄዱበት ጊዜ ወዲያ ወዲህ ሳይሉ፣ ራስ ወደ ዞረበት ወደ ማንኛውም አቅጣጫ ይጓዙ ነበር።

12 ጀርባቸውን፣ እጃቸውን፣ ክንፋቸውን ጨምሮ መላ ሰውነታቸው እንዲሁም አራቱ መንኰራኵሮቻቸው በጠቅላላ በዐይን የተሞሉ ነበሩ።

13 መንኰራኵሮቹም፣ “ተሽከርካሪ መንኰራኵሮች” ተብለው ሲጠሩ ሰማሁ።

14 እያንዳንዱም ኪሩብ አራት አራት ፊት ነበሩት፤ ይኸውም አንደኛው ፊት የኪሩብ፣ ሁለተኛው የሰው ፊት፣ ሦስተኛው የአንበሳ ፊት፣ አራተኛውም የንስር ፊት ነበር።

15 ኪሩቤልም ወደ ላይ ተነሡ፤ እነዚህም በኮቦር ወንዝ አጠገብ ያየኋቸው ሕያዋን ፍጡራን ነበሩ።

16 ኪሩቤል ሲንቀሳቀሱ፣ መንኰራኵሮቹም ከጐናቸው ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ኪሩቤልም ከምድር ለመነሣት ክንፋቸውን ሲዘረጉ፣ መንኰራኵሮቹ ከአጠገባቸው አይለዩም ነበር።

17 ኪሩቤል ቀጥ ብለው በሚቆሙበት ጊዜ እነርሱም ደግሞ ይቆማሉ፤ ኪሩቤል ከምድር ከፍ ከፍ በሚሉበት ጊዜ፣ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ፣ መንኰራኵሮችም ዐብረዋቸው ይነሡ ነበር።

18 ከዚህ በኋላ፣ የእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደሱ ደጃፍ ላይ ተነሥቶ ከኪሩቤል በላይ ቆመ።

19 ኪሩቤልም እኔ እያየኋቸው ክንፎቻቸውን ዘርግተው ከምድር ተነሥተው ሄዱ፤ መንኰራኵሮቹም ዐብረዋቸው ሄዱ፤ በእግዚአብሔርም ቤት በምሥራቁ በር መግቢያ ላይ ቆሙ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበር።

20 እነዚህ በኮቦር ወንዝ አጠገብ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየኋቸው ሕያዋን ፍጡራን ነበሩ፤ ኪሩቤልም እንደ ሆኑ አስተዋልሁ።

21 እያንዳንዳቸው አራት አራት ፊት፣ አራት አራት ክንፍ፣ ከክንፎቻቸውም ሥር የሰውን እጅ የሚመስል ነበራቸው።

22 ፊታቸውም በኮቦር ወንዝ አጠገብ ካየኋቸው ጋራ ይመሳሰል ነበር፤ እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሄድ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告