Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የጓጕንቸር መቅሠፍት

1 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ሄደህ፣ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “እኔን ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።

2 እነርሱን ለመልቀቅ እንቢ ብትል አገርህን ሁሉ በጓጕንቸር መቅሠፍት እመታዋለሁ።

3 አባይ በጓጕንቸሮች ይሞላል፤ ወጥተውም ወደ ቤተ መንግሥትህና ወደ መኝታ ክፍልህ፣ ወደ ዐልጋህም ወደ ሹማምቶችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጆችህና ወደ ቡሖቃዎችህ ይገባሉ።

4 ጓጕንቸሮቹ ወደ አንተና ወደ ሕዝብህ ወደ ሹማምትህም ሁሉ ይመጡባችኋል።” ’ ”

5 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፣ “አሮንን፣ ‘በትርህን ይዘህ በምንጮች፣ በቦዮችና በኵሬዎች ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጕንቸሮችም በግብጽ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ’ ” በለው።

6 አሮንም በግብጽ ውሆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን ሸፈኑ።

7 ሆኖም ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ሠሩ፤ እነርሱም በግብጽ ምድር ላይ ጓጕንቸሮች እንዲወጡ አደረጉ።

8 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ጓጕንቸሮቹን ከእኔና ከሕዝቤ ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ከዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን ትሠዉ ዘንድ ሕዝቡ እንዲሄዱ እፈቅዳለሁ”።

9 ሙሴም ፈርዖንን፣ “በአባይ ወንዝ ካሉት በቀር ከአንተና ከቤቶችህ ጓጕንቸሮቹ እንዲወገዱ ለአንተ፣ ለሹማምትህና ለሕዝብህ የምንጸልይበትን ጊዜ እንድትወስን ለአንተ ትቼዋለሁ” አለው።

10 ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው። ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል።

11 ጓጕንቸሮቹም ከአንተና ከቤቶችህ፣ ከሹማምትህና ከሕዝብህ ተወግደው በአባይ ወንዝ ብቻ ይወሰናሉ።”

12 ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ከተመለሱ በኋላ፣ በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

13 እግዚአብሔር ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየዐጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ።

14 በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች።

15 ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።


የተባይ መቅሠፍት

16 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “አሮንን ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን ትቢያ ምታ’ በለው፤ ከዚያም በግብጽ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ይሆናል” አለው።

17 እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፣ አሮን በትሩን እንደ ያዘ እጁን ሲዘረጋና የምድሩን ትቢያ ሲመታ፣ በግብጽ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። ሰውንም ሆነ እንስሳውን ተናካሽ ትንኝ ወረረው።

18 ነገር ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተናካሽ ትንኞችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልቻሉም። ተናካሽ ትንኞቹም ከሰውና ከእንስሳው ላይ አልወረዱም ነበር።

19 አስማተኞቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር ጣት ነው” አሉት፤ ነገር ግን የፈርዖን ልብ ደንድኖ ስለ ነበር፣ ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አልሰማቸው አለ።


የዝንብ መቅሠፍት

20 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በጧት ተነሥተህ ፈርዖን ወደ ውሃ በሚወርድበት ጊዜ ከፊቱ ቀርበህ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።

21 ሕዝቤ እንዲሄዱ ባትለቅቃቸው፣ በአንተና በሹማምትህ ላይ፣ በሕዝብህና በቤቶችህ ላይ የዝንብ መንጋ እሰድዳለሁ። ያረፉበት መሬት እንኳ ሳይቀር፣ የግብጻውያን ቤቶች ሁሉ ዝንብ ብቻ ይሆናሉ።

22 “ ‘በዚያች ዕለት ግን ሕዝቤ የሚኖርባትን የጌሤምን ምድር የተለየች አደርጋታለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር በዚህች ምድር እንዳለሁ ታውቅ ዘንድ የዝንብ መንጋ በዚያ አይኖርም።

23 በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት አደርጋለሁ፤ ይህ ታምራዊ ምልክት ነገ ይሆናል።’ ”

24 እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ አስጨናቂ የዝንብ መንጋ በፈርዖን ቤተ መንግሥትና በሹማምቱ ቤቶች ላይ ወረደ፤ መላው የግብጽ ምድር ከዝንቡ የተነሣ ተበላሽቶ ነበር።

25 ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ፣ “ሂዱና በዚሁ ምድር ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው።

26 ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ይህ ትክክል አይሆንም፤ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መሥዋዕት በግብጻውያን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ታዲያ በእነርሱ ዐይን አስጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት ብናቀርብ አይወግሩንምን?

27 ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እርሱ እንዳዘዘን መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ መሄድ አለብን።”

28 ፈርዖንም፣ “ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር በምድረ በዳ መሥዋዕት እንድትሠዉ እፈቅድላችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ እንዳትሄዱ። ለእኔም ጸልዩልኝ” አላቸው።

29 ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከአንተ እንደ ተለየሁ ወዲያውኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገም ዝንቡ ሁሉ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ይወገዳል። ብቻ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዲሠዉ ባለመፍቀድ ከዚህ ቀደም ፈርዖን አታልሎ እንዳደረገው አሁንም እንዳያደርግ ርግጠኛ ይሁን።”

30 ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

31 እግዚአብሔር ሙሴ የለመነውን አደረገ። የዝንቡም መንጋ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ተወገደ፤ አንድም ዝንብ እንኳ አልቀረም።

32 በዚህም ጊዜ እንኳ ፈርዖን ልቡን አደነደነ እንጂ፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告