Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ፤ ከኀያሉ እጄ የተነሣ እንዲሄዱ ይለቅቃቸዋል፤ ከኀያሉም እጄ የተነሣ ከአገሩ ያስወጣቸዋል” አለው።

2 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

3 ሁሉን ቻይ አምላክ ሆኜ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅ፣ ለያዕቆብ ተገለጥሁላቸው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በተባለው ስሜ ራሴን አልገለጥሁላቸውም።

4 በእንግድነት የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር እንድሰጣቸው ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቻለሁ።

5 ደግሞም በግብጻውያን ሥር በባርነት ሆነው ያሰሙትን የእስራኤላውያንን የሥቃይ ድምፅ ሰምቻለሁ ኪዳኔንም አስታውሻለሁ።

6 “ስለዚህ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብጻውያን ቀንበር አወጣችኋለሁ። ለእነርሱ ባሪያ ከመሆን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድና በታላቅ ፍርድ እቤዣችኋለሁ።

7 የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ከግብጻውያን ቀንበር ያላቀቅኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላክ መሆኔንም ታውቃላችሁ።

8 ከዚያም ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅ፣ ለያዕቆብ እሰጣችኋለሁ ብዬ ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”

9 ሙሴ ይህን ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ ተስፋ ከመቍረጣቸውና ከአስከፊ እስራታቸው የተነሣ ግን አላደመጡትም።

10 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

11 “ሂድና ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን እስራኤላውያን ከአገሩ እንዲወጡ ይፈቅድላቸው ዘንድ ንገረው።”

12 ሙሴ ግን እግዚአብሔርን፣ “እስራኤላውያን ያልሰሙኝ፣ ፈርዖን እንዴት ይሰማኛል፤ እኔ ለራሴ ተብታባ ሰው ነኝ” አለው።


የሙሴና የአሮን የትውልድ መዝገብ

13 በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ስለ እስራኤላውያንና ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ለሙሴና ለአሮን ነገራቸው፤ እስራኤላውያንንም ከግብጽ እንዲያወጡ አዘዛቸው።

14 የየቤተ ሰቡ አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፣ ሄኖኅ፣ ፈሉስ፣ አስሮን፣ ከርሚ። እነዚህ የሮቤል ነገድ ናቸው።

15 የስምዖን ወንዶች ልጆች፣ ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሐርና የከነዓናዊቱም ልጅ ሳኡል ነበሩ። እነዚህ የስምዖን ነገድ አባቶች ናቸው።

16 በትውልዳቸው መሠረት የሌዊ ወንዶች ልጆች ስሞች እነዚህ ነበሩ፤ ጌርሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ናቸው። ሌዊ መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ።

17 የጌርሶን ወንዶች ልጆች በትውልዳቸው ሎቤኒና ሰሜኢ ነበሩ።

18 የቀዓት ወንዶች ልጆች እንበረም፣ ይስዓር፣ ኬብሮንና ዑዝኤል ነበሩ፤ ቀዓት መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ኖረ።

19 የሜራሪ ወንዶች ልጆች ሞሖሊና ሙሲ ነበሩ። በትውልዳቸው መሠረት የሌዊ ነገዶች እነዚህ ናቸው።

20 እንበረም የአጎቱን እናት ዮካብድን አገባ፤ እርሷም አሮንና ሙሴን ወለደችለት። እንበረም መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ኖረ።

21 የይስዓር ወንዶች ልጆች፣ ቆሬ፣ ናፌግና ዝክሪ ነበሩ።

22 የዑዝኤል ወንዶች ልጆች፣ ሚሳኤል፣ ኤልዳፋንና ሥትሪ ነበሩ።

23 አሮንም የአሚናዳብን ልጅ፣ የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ፤ እርሷም ናዳብንና አብዩድን፣ አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት።

24 የቆሬ ወንዶች ልጆች፣ አሴር፣ ሕልቃናና አብያሳፍ ነበሩ፤ እነዚህ የቆሬ ነገድ ጐሣ ናቸው።

25 የአሮን ልጅ አልዓዛር ከፉትኤል ሴት ልጆች አንዷን አገባ፤ እርሷም ፊንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደየነገዳቸው የሌዋውያን ጐሣዎች አለቆች ነበሩ።

26 እግዚአብሔር “እስራኤላውያንን በየሰራዊታቸው ከግብጽ አውጡ” ብሎ የነገራቸው አሮንንና ሙሴን ነበር።

27 ስለ እስራኤላውያን ከግብጽ መውጣት፣ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን ያናገሩትም እነዚሁ ሙሴና አሮን ነበሩ።

28 እግዚአብሔር ሙሴን በግብጽ በተናገረው ጊዜ፣

29 እንዲህ አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የነገርሁህን ሁሉ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን ንገረው።”

30 ሙሴ ግን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ፈርዖን ምን ብሎ ይሰማኛል? አንደበቴ ኰልታፋ ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告