Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 38 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ
38፥1-7 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥1-8

1 ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ ርዝመቱ ዐምስት ክንድ፣ ወርዱ ዐምስት ክንድ የሆነ ባለአራት ማእዘን ነበረ።

2 ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ አራት ቀንድ ሠሩ፤ መሠዊያውንም በንሓስ ለበጡት።

3 ዕቃዎቹንም ሁሉ ይኸውም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መርጫ ጐድጓዳ ሳሕኖቹን፣ ሜንጦዎቹንና የእሳት መያዣዎቹን ከንሓስ ሠሯቸው።

4 ለመሠዊያውም ከጠርዝ በታች ሆኖ ከመሠዊያው ግማሽ ቁመት ላይ የሚሆን የንሓስ ፍርግርግ ማንደጃ ሠሩ።

5 ለናሱ ፍርግርግ ማንደጃ አራት ማእዘኖች መሎጊያዎቹን እንዲይዙ የንሓስ ቀለበቶችን ሠሩ።

6 መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሠርተው በንሓስ ለበጧቸው።

7 መሠዊያውን ለመሸከም በመሠዊያው ጐኖች ይሆኑ ዘንድ መሎጊያዎቹን በቀለበቶቹ ውስጥ አስገቧቸው፤ ውስጡንም ክፍት በማድረግ ከሳንቃዎች ሠሩት።


የመታጠቢያው ሳሕን

8 የናስ መታጠቢያ ሳሕንና የንሓስ መቆሚያውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ከሚያገለግሉት ሴቶች መስተዋት ሠሩት።


አደባባዩ
38፥9-20 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥9-19

9 ቀጥሎም አደባባዩን ሠሩ፤ የደቡቡ ክፍል ርዝመት አንድ መቶ ክንድ ሲሆን፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤

10 ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የንሓስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹ ላይ ዘንጎች ነበሩት።

11 የሰሜኑም ክፍል ቁመቱ አንድ መቶ ክንድ ነበር፤ ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የንሓስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ነበሩት።

12 የምዕራቡ ጫፍ ወርዱ ዐምሳ ክንድ ነበር፤ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር መቆሚያዎች እንዲሁም የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ያሉት መጋረጃዎች ነበሩት።

13 በፀሓይ መውጫ በኩል ያለው የምሥራቁም ጫፍ ወርዱ ዐምሳ ክንድ ነበር።

14 ከሦስት ምሰሶዎችና ከሦስት መቆሚያዎች ጋራ ርዝመታቸው ዐሥራ ዐምስት ክንድ የሆኑ መጋረጃዎች በአንድ በኩል ባለው መግቢያ ላይ ነበሩ፤

15 ከሦስት ምሰሶዎችና ከሦስት መቆሚያዎች ጋራ ርዝመታቸው ዐሥራ ዐምስት ክንድ የሆኑ መጋረጃዎች በአደባባዩ መግቢያ በሌላው በኩል ነበሩ።

16 በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች በሙሉ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ ነበሩ።

17 የምሰሶዎቹ መቆሚያዎች ንሓስ ነበሩ፤ ኵላቦቹና በምሰሶዎቹ ላይ ያሉት ዘንጎች ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ ጫፎቻቸውም በብር ተለብጠው ነበር፤ ስለዚህ የአደባባዩ ምሰሶዎች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሯቸው።

18 በአደባባዩ መግቢያ ላይ ያለው መጋረጃ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና የጥልፍ ባለሙያ ከጠለፈው፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠራ ነበር፤ ቁመቱ ሃያ ክንድ፣ እንደ አደባባዩ መጋረጃዎች ከፍታው ዐምስት ክንድ ነበረ፤

19 አራት ምሰሶዎችና አራት መቆሚያዎች ነበሩት፤ ኵላቦቻቸውና ዘንጎቻቸው የብር ሲሆኑ፣ ጫፎቻቸው በብር ተለብጠው ነበር።

20 የማደሪያው ድንኳንና የአደባባዩ ዙሪያ ካስማዎች ሁሉ ከንሓስ የተሠሩ ነበሩ።


ለአገልግሎት የዋሉ ዕቃዎች

21 ለማደሪያው ድንኳን፣ ይኸውም ለምስክሩ ድንኳን ሙሴ ባዘዘው፣ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር መሪነት ሌዋውያኑ በጻፉት መሠረት የዕቃዎቹ ቍጥር ይህ ነው።

22 ከይሁዳ ነገድ የሆር የልጅ ልጅ፣ የኡሪ ልጅ የሆነው ባስልኤል፣ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።

23 ከርሱም ጋራ ከዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ፣ ዕቅድ አውጭና የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ጥልፍ ጠላፊ ነበር።

24 ለመቅደሱ ሥራ ሁሉ ከመወዝወዙ ስጦታ በመቅደሱ ሰቅል መሠረት የዋለው ጠቅላላ ወርቅ ሃያ ዘጠኝ መክሊትና ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ።

25 በቈጠራው ወቅት ተቈጥረው ከነበሩት ማኅበረ ሰብ የተገኘው ብር ለመቅደሱ ሰቅል አንድ መቶ መክሊትና አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሰባ ዐምስት ሰቅሎች ነበሩ።

26 ከተቈጠሩት ጋራ ዐብረው ከሆኑት ሃያና ከሃያ ዓመት በላይ የሆናቸው ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ሰዎች የሰጡት እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን በአንድ ሰው አንድ ቤካ ይኸውም ግማሽ ሰቅል ነበረ።

27 አንድ መቶ የብር መክሊቶች የመቅደሱንና የመጋረጃዎቹን መቆሚያዎች ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር፤ ይኸውም ከአንድ መቶ መክሊቶች አንድ መቶ መቆሚያዎች ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ መቆሚያ አንድ መክሊት ማለት ነው።

28 አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሰባ ዐምስት ሰቅሎችን ለምሰሶዎቹ ኵላቦች፣ የምሰሶዎቹን ዐናት ለመለበጥና ዘንጎቻቸውንም ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር።

29 ከመወዝወዙ ስጦታ የሆነው ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺሕ አራት መቶ ሰቅል ነበረ።

30 ለመገናኛው ድንኳን መግቢያ ለናስ መሠዊያው ከናስ መጫሪያው፣ ለዕቃዎቹም ሁሉ መቆሚያዎቹን ለመሥራት አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር፤

31 ለአደባባዩ ዙሪያ፣ ለመግቢያው እንዲሁም ለማደሪያው ድንኳን ካስማዎች ሁሉና ለአደባባዩ ዙሪያ ሁሉ እንዲሁ አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告