Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 36 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ስለዚህ የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ሁሉ እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው እግዚአብሔር ጥበብንና ችሎታን የሰጣቸው፣ ባስልኤል፣ ኤልያብና ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ሥራውን ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ይሥሩት።”

2 ከዚያም ሙሴ ባስልኤልንና ኤልያብን እንዲሁም እግዚአብሔር ችሎታ የሰጣቸውን፣ መጥተው ሥራውን ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑትን ጥበብ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ አስጠራ።

3 የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ለማከናወን እስራኤላውያን ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ተቀበሉ፤ ሕዝቡ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን በየማለዳው ማምጣታቸውን ቀጠሉ።

4 ስለዚህ የመቅደሱን ሥራ ሁሉ ይሠሩ የነበሩ ጥበበኞች የሆኑ ባለሙያዎች ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፤

5 ሙሴንም፣ “ሕዝቡ እግዚአብሔር እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ እያመጡ ነው” አሉት።

6 ከዚያም ሙሴ ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህንም ቃል ወደ ሰፈሩ ላኩት፤ “ማንም ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ሌላ ምንም ስጦታ ማድረግ የለበትም፤” ስለዚህ ሕዝቡ ትርፍ እንዳያመጡ ተከለከሉ፤

7 ምክንያቱም ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በእጃቸው ያለው ከበቂ በላይ ነበረ።


የማደሪያው ድንኳን
36፥8-38 ተጓ ምብ – ዘፀ 26፥1-37

8 የሥራ ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የማደሪያውን ድንኳን በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በጥልፍ ዐዋቂ፣ ኪሩቤል ከተጠለፉበት ከዐሥር መጋረጃዎች ሠሩት።

9 መጋረጃዎቹም ሁሉ ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ሲሆን፣ ቁመታቸው ሃያ ስምንት ክንድ፣ ወርዳቸው አራት ክንድ ነበር።

10 ዐምስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ በማጋጠም ሰፏቸው፤ የቀሩትን ዐምስቱንም እንዲሁ አደረጉ።

11 ተጋጥሞ ከተሰፋው መጋረጃ ጠርዝ ጫፍ ላይ ከሰማያዊ ግምጃ ቀለበቶችን አበጁ፤ ተጋጥሞ በተሰፋው በሌላው መጋረጃ ጫፍ ላይም ተመሳሳይ ነገር አደረጉ።

12 በአንደኛው መጋረጃ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን በሌላው ተጋጥሞ ከተሰፋው በስተመጨረሻ ካለው መጋረጃ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን እርስ በርሳቸው ትይዩ በማድረግ ሠሩት።

13 ከዚያም ዐምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሠሩ፤ የማደሪያው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድም ተጋጥመው የተሰፉትን ሁለቱን መጋረጃዎች አያያዙባቸው።

14 ከማደሪያው በላይ ለሚሆነው ድንኳን ከፍየል ቈዳ የተሠሩ በጠቅላላ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ሠሩ።

15 ዐሥራ አንዱ መጋረጃዎች ተመሳሳይ ልክ ሲኖራቸው፣ ቁመታቸው ሠላሳ ክንድ፣ ወርዳቸውም አራት ክንድ ነበር።

16 ዐምስቱን መጋረጃዎች በአንድ በኩል፣ ሌሎቹን ስድስት መጋረጃዎች ደግሞ በሌላ በኩል አንድ ላይ አያያዟቸው።

17 በስተመጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን፣ በሌላ በኩል ባለው በስተመጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ ዐምሳ ቀለበቶችን አበጁ።

18 ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝም ዐምሳ የንሓስ ማያያዣዎችን ሠሩ።

19 ከዚያም ለድንኳኑ መሸፈኛ የሚሆን ቀይ ከተነከረ የአውራ በግ ቈዳ ሠሩ፤ በላዩ ላይ የሚሆንም የአቆስጣ ቈዳ አበጁ።

20 ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አበጁ።

21 እያንዳንዱም ወጋግራ ቁመቱ ዐሥር ክንድ፣ ስፋቱ አንድ ክንድ ተኩል ነበር፤

22 ትይዩ የሆኑ ሁለት ጕጦች ነበሩት፤ የማደሪያውን ድንኳን ወጋግራዎች በዚህ መልክ ሠሩ።

23 በደቡብ በኩል ላለው የማደሪያው ድንኳን ሃያ ወጋግራዎችን አበጁ፤

24 ለእያንዳንዱ ጕጠት አንድ መቆሚያ፣ ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያ ሆኖ አርባ የብር መቆሚያዎችን አበጁ።

25 በስተሰሜን በኩል ላለው የማደሪያው ድንኳን ሃያ ወጋግራዎችን ሠሩ፤

26 ለእያንዳንዱ ወጋግራ ሁለት መቆሚያ የሆኑ አርባ የብር መቆሚያዎችን ሠሩ።

27 በዳር በኩል ይኸውም በስተምዕራብ ጫፍ ባለው ማደሪያው ድንኳን ስድስት ወጋግራዎችን ሠሩ።

28 ዳርና ዳር ላሉት የማደሪያው ድንኳን ማእዘኖችም ሁለት ወጋግራዎችን ሠሩ።

29 በእነዚህ ሁለት ማእዘኖች ላይ ከታች አንሥቶ እስከ ላይ ድረስ ወጋግራዎቹ በአንድ ላይ ተነባብረው በአንድ ቀለበት ውስጥ ተገጥመው ነበር፤ ሁለቱም አንድ አካል ሆነው ተሠርተው ነበር።

30 ስለዚህ ስምንት ወጋግራዎችና ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያዎች ሆነው ዐሥራ ስድስት የብር መቆሚያዎች ነበሩ።

31 እንደዚሁም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን ሠሩ፤ በማደሪያው ድንኳን በአንድ በኩል ላሉት ወጋግራዎች ዐምስት አግዳሚዎችን ሠሩ፤

32 በሌላ በኩል ላሉት ዐምስት አግዳሚዎች፣ በምዕራብ በኩል በማደሪያው ድንኳን ዳር ላይ ላሉት ወጋግራዎች ዐምስት አግዳሚዎችን ሠሩ።

33 በወጋግራዎቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር እንዲዘረጋ ሆኖ መካከለኛውን አግዳሚ ሠሩ።

34 ወጋግራዎቹን በወርቅ ለበጧቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝም የወርቅ ቀለበቶችን ሠሩ፤ እንዲሁም አግዳሚዎቹን በወርቅ ለበጧቸው።

35 ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ፣ እጀ ጥበብ ባለሙያም ኪሩቤል የተጠለፉበት መጋረጃ ሠራ።

36 ለርሱም አራት ምሰሶዎች ከግራር ዕንጨት ሠርተው በወርቅ ለበጧቸው፤ ለእነርሱም አራት የወርቅ ኵላቦችንና አራት የብር መቆሚያዎችን አበጁላቸው።

37 በድንኳኑ መግቢያ ጥልፍ ጠላፊ እንደሚሠራው ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አበጁለት፤

38 ለእነርሱም ኵላቦች ያሏቸው ዐምስት ምሰሶዎች ሠሩላቸው፤ የምሰሶዎቹን ዐናቶችና ዘንጎች በወርቅ በመለበጥ ዐምስቱን መቆሚያዎች ከንሓስ ሠሩ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告