Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 35 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሰንበት ሥርዐቶች

1 ሙሴ የእስራኤልን ማኅበረ ሰብ ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር እንድትፈጽሟቸው ያዘዛችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤

2 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የሰንበት ዕረፍት፣ የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ በዕለቱ ማንኛውንም ዐይነት ሥራ የሚሠራ ቢኖር ሞት ይገባዋል።

3 በሰንበት ቀን በማናቸውም መኖሪያዎቻችሁ ውስጥ እሳት አታንድዱ።”


ለመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች
35፥10-19 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥32-41

4 ሙሴ ለእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤

5 ካላችሁ ንብረት ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርቡ፤ ፈቃደኛ የሆነ ማንም ለእግዚአብሔር፦ “የወርቅ፣ የብር፣ የናስ መባ ያምጣ።

6 ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ፤ ቀጭን ሐር፣ የፍየል ጠጕር፣

7 ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ፣ እንዲሁም የለፋ ቈዳ፣ የግራር ዕንጨት፤

8 ለመብራት የወይራ ዘይት፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ መዐዛ ላለው ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞች፤

9 በኤፉዱና በደረት ኪስ ላይ የሚሆኑ መረግዶችና ሌሎች ዕንቍዎችን መባ አድርጎ ያምጣ።

10 “በመካከላችሁ ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ይሥሩ፦

11 “የመገናኛውን ድንኳን ከነድንኳኑና ከነመደረቢያው፣ ማያያዣዎችን፣ ክፈፎችን፣ አግዳሚዎችን፣ ቋሚዎችንና መሠረቶችን፤

12 ታቦቱን ከነመሎጊያዎቹ፣ የስርየት መክደኛውንና የሚሸፍነውን መጋረጃ፤

13 ጠረጴዛውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ዕቃዎቹን ሁሉና የገጸ ኅብስቱን፤

14 ለመብራት የሆነውን መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ ቀንዲሎችንና ለመብራት የሚሆነውን ዘይት፤

15 የዕጣን መሠዊያውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ቅብዐ ዘይቱንና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን፤ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ የሚሆነውን የመግቢያ መጋረጃ፤

16 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከንሓስ መጫሪያው፣ መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣ የንሓስ ሰኑን ከነማስቀመጫው፣

17 የአደባባዩን መጋረጃዎች ከነምሰሶዎቻቸውና ከነመሠረቶቹ፣ የአደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፤

18 ለመገናኛው ድንኳንና ለአደባባዩ የሚሆኑ የድንኳን ካስማዎችና ገመዶቻቸው፤

19 በመቅደሱ ውስጥ ለማገልገል የሚለበሱ የፈትል ልብሶችን ይኸውም የካህኑ የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንዶች ልጆቹን ልብሶች ይሥሩ።”

20 ከዚያም የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ፤

21 ፈቃደኛ የነበረና ልቡን ያነሣሣው ሁሉ በመምጣት ለመገናኛው ድንኳን ሥራ፣ ለአገልግሎቱ ሁሉና ለተቀደሱ ልብሶች የሚሆን ለእግዚአብሔር መባ አመጡ።

22 ፈቃደኛ የነበሩ ሁሉ፣ ወንዶችም ሴቶችም መጥተው ከሁሉም ዐይነት የወርቅ ጌጦች አመጡ፤ የአፍንጫ ጌጦችን፣ ሎቲዎችን፣ ቀለበቶችን፣ ድሪዎችንና ጌጣጌጦችን ሁሉ አመጡ፤ ሁሉም ወርቃቸውን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ።

23 ሰማያዊ፣ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን ሐር ወይም የፍየል ጠጕር፣ ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ ወይም የአቆስጣ ቈዳ አመጡ።

24 የብር ወይም የናስ መባ ማቅረብ የቻሉ ሁሉ ለእግዚአብሔር መባ አድርገው አመጡ፤ የግራር ዕንጨት ያለው ሁሉ አስፈላጊ በሆነው ሥራ እንዲውል አመጣው።

25 ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ፤ የፈተሉትንም ሰማያዊ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን በፍታ አመጡ።

26 ፈቃደኛ የነበሩና ጥበቡ ያላቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ጠጕር ፈተሉ።

27 መሪዎቹም ኤፉድና በደረት ኪሱ ላይ እንዲሆን የከበሩ ድንጋዮችንና ሌሎች ዕንቍዎች አመጡ።

28 እንዲሁም ለመብራቱ፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ ሽታ ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞችንና የወይራ ዘይትን አመጡ።

29 ፈቃደኛ የሆኑ እስራኤላውያን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ እግዚአብሔር በሙሴ በኩል እንዲያከናውኑት ላዘዛቸው ሥራ ሁሉ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን ለእግዚአብሔር አመጡ።


ባስልኤልና ኤልያብ
35፥30-35 ተጓ ምብ – ዘፀ 31፥2-6

30 ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን አላቸው፤ “እነሆ፤ እግዚአብሔር ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሑር ልጅ፣ የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጧል።

31 በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማንኛውም ዐይነት ሙያ የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞልቶበታል፤

32 ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በንሓስ የጥበብ ሥራ እንዲሠራ ነው፤

33 ድንጋዮችን እንዲጠርብና እንዲያወጣ፣ የዕንጨት ሥራ እንዲሠራና ማንኛውንም ዐይነት የጥበብ ሙያ እንዲያከናውን ነው።

34 እንዲሁም ለርሱና ከዳን ነገድ ለሆነው ለአሂሳሚክ ልጅ ለኤልያብ፣ ለሁለቱም ሌሎችን የማስተማር ችሎታ ሰጣቸው።

35 የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ዕቅድ አውጭዎች፣ በሰማያዊ በሐምራዊና በቀይ ማግ፣ በቀጭን ሐር ጥልፍ ጠላፊዎችና ፈታዮች፤ ሁሉም ዋና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ዕቅድ አውጭዎች በመሆን ማንኛውንም ዐይነት ሥራ ያከናውኑ ዘንድ በጥበብ ሞልቷቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告