Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 31 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ባስልኤልና ኤልያብ
31፥2-6 ተጓ ምብ – ዘፀ 35፥30-35

1 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጬዋለሁ።

3 በጥበብ፣ በብልኀት፣ ዕውቀትና ማንኛውንም ዐይነት ሙያ እንዲኖረው የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞልቼዋለሁ።

4 ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በንሓስ ለሚሠሩት ሥራዎች በጥበብ የተሠሩ ጌጦችን እንዲያበጅ፣

5 ድንጋዮችን እንዲቈፍርና እንዲጠርብ ከዕንጨትም ጥርብ እንዲያወጣ፣ ሁሉንም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራዎችን እንዲያከናውን ነው።

6 በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን እንዲረዳው መርጬዋለሁ። “እንዲሁም ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ለእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ብልኀትን ሰጥቻቸዋለሁ፤

7 “ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን፣ የምስክሩን ታቦት በላዩ ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው ጋራ፣ ሌሎች የድንኳኑን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፣

8 ጠረጴዛውን ከነዕቃዎቹ፣ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን የወርቅ መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ የዕጣኑን መሠዊያ፣

9 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከነዕቃዎቹ፣ ሰኑን፣ ከነማስቀመጫው፣

10 ከፈትል የተሠሩ ልብሶችን ይኸውም የካህኑን የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንድ ልጆቹ ልብሶች፣

11 እንዲሁም የመቅደሱ የሆነውን ቅብዐ ዘይትና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን እንዲሠሩ ነው። “ልክ እኔ እንዳዘዝሁህ ያብጇቸው።”


ሰንበት

12 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

13 “ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ምልክት ይሆናል፤ ይኸውም የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንድታውቁ ነው።

14 “ ‘ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን አክብሩ፤ ማንም ቢያረክሰው በሞት ይቀጣል፤ በዚያ ቀን ማንም የሚሠራ ቢኖር ከወገኑ ተነጥሎ ይለይ።

15 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን ማንም ቢሠራ በሞት መቀጣት አለበት።

16 እስራኤላውያን በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ሰንበትን በመጠበቅ የዘላለም ኪዳን አድርገው ማክበር አለባቸው፤

17 በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ሠርቶ፣ በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፏልና።’ ”

18 እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ መናገሩን ከፈጸመ በኋላ፣ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላት፣ ሁለቱን የምስክር ጽላት ለርሱ ሰጠው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告