ዘፀአት 30 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየዕጣን መሠዊያ 30፥1-5 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥25-28 1 “ዕጣን የሚጤስበት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ። 2 ርዝመቱና ጐኑ ባለአንድ አንድ ክንድ የሆነ ከፍታውም ሁለት ክንድ የሆነ አራት ማእዘን ይሁን፤ ከመሠዊያው ጋራ አንድ ወጥ የሆኑ ቀንዶች ይኑሩት። 3 ላዩን፣ ጐኖቹን ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለብጣቸው፤ ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ አብጅለት። 4 መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች የሚይዙ፣ ከክፈፉ በታች ትይዩ የሆኑ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ለመሠዊያው አብጅ። 5 መሎጊያዎቹንም ከግራር ዕንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 6 መሠዊያውን ከመጋረጃው ፊት ለፊት፣ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት፣ ከምስክሩ በላይ ካለው እኔ አንተን ከምገናኝበት ከስርየት መክደኛው ፊት አስቀምጠው። 7 “አሮን መብራቶቹን በሚያዘጋጅበት ጊዜ፣ በየማለዳው ደስ የሚያሰኝ ሽታ ዕጣን በመሠዊያው ላይ ያጢስ። 8 ምሽት ላይ መብራቶቹን በሚያበራበትም ጊዜ ዕጣኑን ማጠን አለበት፤ ይኸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ዕጣኑ በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር እንዲጤስ ነው። 9 በዚህም መሠዊያ ላይ ሌላ ዕጣን ወይም ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መሥዋዕት አታቅርብ፤ የመጠጥ መሥዋዕትም አታፍስስበት። 10 አሮን በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርግበታል፤ ይህ ዓመታዊ ማስተስረያ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለማስተስረያ ከሚሆን የኀጢአት መሥዋዕት ደም ጋራ መደረግ አለበት፤ ይህም ለእግዚአብሔር እጅግ ቅዱስ ነው።” የማስተስረያ ገንዘብ 11 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 12 “የእስራኤላውያንን ጠቅላላ ቈጠራ በምታደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በሚቈጠርበት ወቅት ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆን ወጆ ለእግዚአብሔር መክፈል አለበት፤ በዚህም ዐይነት ስትቈጥራቸው በእነርሱ ላይ መቅሠፍት አይመጣም። 13 ማንም ወደ ተቈጠሩት ዘንድ የሚያልፍ ሃያ አቦሊ በሚመዝን በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግማሽ ሰቅል መስጠት አለበት፤ ይህ ግማሽ ሰቅል ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። 14 ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከሃያ በላይ ሆኖ ወደ ተቈጠሩት ያለፉት ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸው። 15 ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ ባለጠጋው ከግማሽ ሰቅል በላይ፣ ድኻውም አጕድሎ አይስጥ። 16 የማስተስረያውን ገንዘብ ከእስራኤላውያን ተቀብለህ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት አውለው፤ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት የእስራኤላውያን ማስተስረያ ይሆናል።” የመታጠቢያ ሰን 17 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 18 “ለመታጠቢያ ከንሓስ ማስቀመጫው ጋራ የንሓስ መቆሚያ አብጅ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ አድርግበት። 19 አሮንና ወንዶች ልጆቹ በውስጡ ባለው ውሃ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል። 20 ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ሁሉ እንዳይሞቱ በውሃ ይታጠቡ፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የእሳት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ለማገልገል በሚቀርቡበት ጊዜ፣ 21 እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠባሉ፤ ይህም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለአሮንና ለትውልዶቹ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።” ቅብዐ ዘይት 22 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፣ 23 “ምርጥ ቅመሞችን፣ ዐምስት መቶ ሰቅል ፈሳሽ ከርቤ፣ ግማሽ ይኸውም ሁለት መቶ ዐምሳ ሰቅል ጣፋጭ ቀረፋ፣ ሁለት መቶ ዐምሳ ሰቅል ከሙን፣ 24 ዐምስት መቶ ሰቅል ብርጕድ ውሰድ፤ ሁሉም እንደ መቅደሱ ሰቅልና አንድ የሂን መስፈሪያ የወይራ ዘይት ይሁን፤ 25 እነዚህን በቀማሚ እንደ ተሠራ እንደሚሸት ቅመም የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት አድርግ፤ የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት ይሆናል። 26 ከዚያም የመገናኛውን ድንኳን፣ የምስክሩን ታቦት፣ ቅባ። 27 ጠረጴዛውንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣ መቅረዙንና ዕቃዎቹን፣ የዕጣን መሠዊያውን ቅባ። 28 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሰኑን ከነመቆሚያው እንድትቀባበት ይሁን። 29 እጅግ የተቀደሱ ይሆኑም ዘንድ ቀድሳቸው፤ የሚነካቸውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል። 30 “ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ቅባቸው፤ ቀድሳቸውም። 31 ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ይህ የእኔ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሆናል። 32 በማንም ሰው ሰውነት ላይ አታፍስሱት፤ በተመሳሳይ መንገድ ምንም ዘይት አትሥሩ፤ የተቀደሰ ነው፤ ቅዱስ መሆኑን ልብ በሉ። 33 ተመሳሳይ ዐይነት የሠራና ከካህናት ሌላ በማንም ሰው ላይ ያፈሰሰ ሁሉ ከወገኑ ይወገድ።’ ” ዕጣን 34 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ተመጣጣኝ በማድረግ የጣፋጭ ሽቱ ቅመሞች፣ የሚንጠባጠብ ሙጫ፣ በዛጐል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፣ የሚሸት ሙጫ እና ንጹሕ ዕጣን ወስደህ፣ 35 በቀማሚ እንደ ተሠራ ጣፋጭ መዐዛ ያለው የተቀመመ ዕጣን አብጅ፤ በጨው የተቀመመ፣ ንጹሕና የተቀደሰ ይሁን። 36 ከርሱም ጥቂቱን ወቅጠህ ዱቄት በማድረግ አልመህ በመገናኛው ድንኳን ከምስክሩ ፊት ለፊት ከአንተ ጋራ በምገናኝበት ስፍራ አስቀምጠው፤ ለአንተ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። 37 ለራስህ በዚያ ዐይነት መንገድ ምንም ዐይነት ዕጣን አታብጅ። ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መሆኑን ልብ በል። 38 በመልካም ሽታው ይደሰት ዘንድ እርሱን አስመስሎ የሚሠራ ሁሉ ከወገኑ የተወገደ ይሁን።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.