ዘፀአት 28 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምልብሰ ተክህኖ 1 “ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ከእስራኤላውያን መካከል ወንድምህ አሮንን ከወንዶች ልጆቹ ከናዳብ፣ ከአብዩድ፣ ከአልዓዛርና ከኢታምር ጋራ ወደ አንተ አቅርባቸው። 2 ለርሱም ማዕርግና ክብር ለመስጠት ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን አብጅለት። 3 ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ የተለየ ይሆን ዘንድ ጥበብ ለሰጠኋቸው በዚህ ጕዳይ ላይ ጥበበኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ለአሮን መጐናጸፊያዎችን እንዲሠሩለት ንገራቸው። 4 የሚሠሯቸው መጐናጸፊያዎች የደረት ልብስ ኤፉድ ቀሚስ፣ ጥልፍ ሸሚዝ፣ ጥምጥምና መታጠቂያ ናቸው፤ ካህን ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ይሠራሉ። 5 ወርቅ፣ ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ቀጭን በፍታ ይጠቀሙ። ኤፉድ 28፥6-14 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥2-7 6 “የጥልፍ ዐዋቂዎች ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ ይሥሩት። 7 መተሳሰር እንዲችል ሆኖ፣ ዳርና ዳር ከሚገኙት ከሁለቱ ጐኖች ጋራ የተያያዙ ሁለት የትከሻ ንጣዮች ይኑሩት። 8 በጥበብ የተጠለፈው የወገብ መታጠቂያ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር ከኤፉድ ጋራ አንድ ወጥ ሆኖ የተሠራ ይሁን። 9 “ሁለት የመረግድ ድንጋዮች ውሰድና የእስራኤልን ልጆች ስሞቻቸውን ቅረጽባቸው። 10 እንደ ልደታቸው ቅደም ተከተል ስድስቱን ስሞች በአንዱ ድንጋይ ላይ የቀሩትንም ስሞች በሌላው ላይ ቅረጽባቸው። 11 የእጅ ጥበብ ባለሙያ ማኅተም እንደሚቀርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለቱ ድንጋዮች ላይ ቅረጽ፤ ከዚያም ድንጋዮቹን በወርቅ ፈርጥ ክፈፋቸው፤ 12 ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ጋራ አያይዛቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት መታሰቢያ እንዲሆኑ አሮን ስሞቹን በትከሻው ላይ ይሸከማቸው። 13 የወርቅ ፈርጦችን አብጅ፤ 14 እንደ ገመድ ያሉ ሁለት በንጹሕ ወርቅ የተጐነጐኑ ድሪዎችን አብጅተህ ከፈርጡ ጋራ አያይዛቸው። የደረት ኪስ 28፥15-28 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥8-21 15 “የፍርድ መስጫውን የደረት ኪስ ብልኅ ሠራተኛ እንደሚሠራው አድርገህ አብጀው፤ ልክ እንደ ኤፉዱ ከወርቅ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ አብጀው። 16 ርዝመቱ አንድ ስንዝር፣ ወርዱም አንድ ስንዝር ሆኖ ባለአራት ማእዘንና በድርቡ የታጠፈ ይሁን። 17 ከዚያም በላዩ ላይ በአራት ረድፍ የከበሩ ድንጋዮች አድርግበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮን፣ የሚያበረቀርቅ ዕንቍ፤ 18 በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፣ ሰንፔርና፣ አልማዝ፤ 19 በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፣ ኬልቄዶንና፣ አሜቴስጢኖስ፤ 20 በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያሰጲድ አድርግበት፤ በወርቅ ፈርጥም ክፈፋቸው። 21 የዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስሞች እንደ ማኅተም የተቀረጸባቸው ለእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ይሁኑ። 22 “ለደረት ኪሱ ከንጹሕ ወርቅ እንደ ገመድ ሆኖ የተጌጠ ጕንጕን አብጅለት። 23 ለርሱም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አብጅተህ ከደረት ኪሱ ሁለት ጐኖች ጋራ አያይዘው። 24 ሁለቱን የወርቅ ጕንጕኖች በደረት ኪሱ ጐኖች ላይ ካሉት ቀለበቶች ጋራ አያይዛቸው። 25 ሌሎቹን የጕንጕን ጫፎች በፊት ላይ ካለው ኤፉድ በትከሻው ላይ ካሉት ንጣዮች ጋራ በማጋጠም ከሁለቱ የወርቅ ፈርጦች ጋራ አያይዛቸው። 26 ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አበጅተህ ከኤፉዱ ቀጥሎ ባለው በውስጠኛ ጠርዝ ላይ፣ በሌላ በኩል ካሉት ሁለት የደረት ኪስ ጐኖች ጋራ አያይዛቸው። 27 ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶች አበጅተህ ከኤፉዱ መታጠቂያ ከፍ ብሎ ከመጋጠሚያው አጠገብ ካለው በኤፉዱ ፊት ለፊት፣ በትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ግርጌ ጋራ አያይዘው። 28 የደረት ኪሱም ቀለበቶች፣ የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ጋራ እንዳይላቀቅ፣ ከመታጠቂያው ጋራ በማገናኘት በሰማያዊ ገመድ ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋራ ይያያዙ። 29 “አሮን ወደ መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርድ መስጫው ደረት ኪስ በልቡ ላይ ይሸከም። 30 ወደ እግዚአብሔር ፊት በሚገባበት ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆኑ ዘንድ ኡሪሙንና ቱሚሙን በደረት ኪሱ አድርግ፤ ስለዚህ አሮን ሁልጊዜ ለእስራኤላውያን የፍርድ መስጫውን በእግዚአብሔር ፊት በልቡ ላይ ይሸከማል። ሌሎቹ አልባሳት 28፥31-43 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥22-31 31 “የኤፉዱ ቀሚስ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ጨርቅ ይሁን፤ 32 ከላይ በኩል በመካከሉ ዐንገትጌ አድርገህ አብጀው፤ እንዳይቀደድም በማስገቢያው ዙሪያ እንደ ክሳድ ያለ ዝምዝም ጠርዝ ሥራለት። 33 በጨርቁ ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ ሮማኖቹን፣ በመካከሉም የወርቅ ሻኵራዎችን አብጅ። 34 የወርቅ ሻኵራዎቹና ሮማኖቹ በጨርቁ ጠርዝ ዙሪያ በመፈራረቅ ይሆናሉ። 35 አሮንም በአገልግሎቱ ጊዜ ይህን መልበስ አለበት፤ በእግዚአብሔር ፊት ወደ መቅደሱ በገባና ከመቅደሱ ሲወጣ እንዳይሞት የሻኵራዎቹ ድምፅ ይሰማል። 36 “ከንጹሕ ወርቅ ዝርግ ሳሕን አበጅተህ፣ ቅዱስ ለእግዚአብሔር በማለት በማኅተም ላይ እንደሚቀረጽ ቅረጸው። 37 ከመጠምጠሚያው ጋራ እንዲያያዝ ሰማያዊ ፈትል እሰርበት፤ እርሱም በመጠምጠሚያው ፊት በኩል ይሁን። 38 ይህም በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል፤ እስራኤላውያን ለይተው በሚያቀርቧቸው በማናቸውም የተቀደሱ ስጦታዎች ውስጥ ያለውን በደል ይሸከማል፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሁልጊዜ በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል። 39 “ሸሚዙን ከቀጭን በፍታ ሥራ፤ መጠምጠሚያውንም ከቀጭን በፍታ አብጀው፤ መታጠቂያውንም ጥልፍ ጠላፊ የሠራው ይሁን። 40 የአሮን ወንድ ልጆች ክብርና ማዕርግ እንዲኖራቸው ሸሚዞችን፣ መታጠቂያዎችን፣ የራስ ማሰሪያዎችን አብጅላቸው። 41 እነዚህን ልብሶች ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ካለበስህ በኋላ ቅባቸው፤ ካናቸው፤ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝም ዘንድ ቀድሳቸው። 42 “ከወገብ ጀምሮ እስከ ጭን የሚደርስ ሰውነትን የሚሸፍን ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ቍምጣ አብጅ። 43 አሮንና ወንድ ልጆቹ ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ወይም በመቅደሱ ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ፣ በደል ፈጽመው እንዳይሞቱ እነዚህን መልበስ አለባቸው። “ለአሮንና ለትውልዶቹ ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.