Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 27 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረቢያ መሠዊያ
27፥1-8 ተጓ ምብ – ዘፀ 38፥1-7

1 “ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ ርዝመቱ ዐምስት፣ ወርዱም ዐምስት ክንድ ሆኖ ባለአራት ማእዘን ይሁን።

2 ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ ቀንድ አድርግለት፤ መሠዊያውንም በንሓስ ለብጠው።

3 ዕቃዎቹን ሁሉ ይኸውም የዐመድ ማስወገጃ ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፣ ሜንጦዎችንና የፍም መያዣዎችን ከንሓስ አብጃቸው።

4 ዐመድ ማውረጃ የሚሆን እንደ መረብ የሆነ የንሓስ ፍርግርግ አድርግለት በአራቱም የመረብ ማእዘኖች ላይ የንሓስ ቀለበቶች አብጅ።

5 እስከ መሠዊያው ወገብ እንዲደርስ በመሠዊያው ዙሪያ ባለው እርከን ሥር አድርገው።

6 የግራር ዕንጨት መሎጊያዎችን ለመሠዊያው ሠርተህ በንሓስ ለብጣቸው።

7 በሸክም ጊዜ በመሠዊያው ሁለቱም ጐኖች እንዲሆኑ፣ መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ።

8 መሠዊያውን ውስጡን ባዶ ከሆኑ ሳንቃዎች አብጀው፤ ልክ በተራራው ላይ ባየኸው መሠረት ይበጅ።


የመገናኛው ድንኳን አደባባይ
27፥9-19 ተጓ ምብ – ዘፀ 38፥9-20

9 “ለመገናኛው ድንኳን አደባባይ አብጅለት፤ በደቡብ በኩል ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ይሁን፤ ከቀጭን በፍታ የተፈተሉ መጋረጃዎች፣

10 ሃያ ምሰሶዎች፣ ሃያ የንሓስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ይኑሩት።

11 በሰሜኑም በኩል አንድ መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይሁኑ፤ ሃያ ምሰሶዎቹ፣ ሃያ የንሓስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎችም ላይ ዘንጎች ይኑሩ።

12 “የአደባባዩ ምዕራብ ጫፍ ስፋቱ ዐምሳ ክንድ ሆኖ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር መቆሚያዎች ያሉት መጋረጃዎች ይኑሩት።

13 በምሥራቅ ጫፍ በፀሓይ መውጫ በኩል ያለው አደባባይ አሁንም ዐምስት ክንድ ስፋት ይኑረው።

14 ሦስት ምሰሶዎችና ሦስት መቆሚያዎች ያሏቸው ርዝመታቸው ዐሥራ ዐምስት ክንድ የሆነ መጋረጃዎች በአንድ በኩል ባለው ደጃፍ ይሁኑ።

15 ሦስት ምሰሶዎች ሦስት መቆሚያዎች ያሏቸው ርዝመታቸው ዐሥራ ዐምስት ክንድ የሆነ መጋረጃዎች በሌላው በኩል ይሁኑ።

16 “ለአደባባዩ መግቢያ አራት ምሰሶዎችና አራት መቆሚያዎች ያሉት ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና ከቀጭን በፍታ የተፈተለ፣ ጥልፍ ጠላፊ የጠለፈበት ሃያ ክንድ ርዝመት ያለው መጋረጃ ይሁን።

17 በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት ምሰሶዎች ሁሉ የብር ዘንጎች፣ ኵላቦችና የንሓስ መቆሚያዎች ይኑሯቸው።

18 አደባባዩ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ፣ ስፋቱ ዐምሳ ክንድ ሆኖ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ማግ ቁመታቸው ዐምስት ክንድ የሆነ መጋረጃዎችና የንሓስም መቆሚያዎች ያሉት ይሁን።

19 ጥቅማቸው ምንም ዐይነት ይሁን፣ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት የሚውሉ ዕቃዎች በሙሉ የድንኳኑና የአደባባዩ ካስማዎችም ሁሉ ሳይቀሩ ከንሓስ የተሠሩ ይሁኑ።


የመቅረዙ ዘይት
27፥20-21 ተጓ ምብ – ዘሌ 24፥1-3

20 “መብራቶቹ ያለማቋረጥ እንዲያበሩ ለመብራቱ የሚሆን ከወይራ ተጨምቆ የተጠለለ ንጹሕ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው።

21 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከመጋረጃው በስተውጭ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት ለፊት፣ አሮንና ወንድ ልጆቹ መብራቶቹን ከምሽት እስከ ንጋት በእግዚአብሔር ፊት እንዲበሩ ያድርጉ፤ ይህም በእስራኤላውያን ዘንድ ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告