Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 26 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የማደሪያው ድንኳን
26፥1-37 ተጓ ምብ – ዘፀ 36፥8-38

1 “በቀጭኑ ከተፈተለ የበፍታ ድርና በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ በተሠሩ ዐሥር መጋረጃዎች ማደሪያ ድንኳኑን ሥራ፤ እጀ ብልኅ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍባቸው።

2 መጋረጃዎች ሁሉ እኵል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሃያ ስምንት ክንድ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን።

3 ዐምስቱን መጋረጃዎች አገጣጥመህ ስፋ፤ የቀሩትንም ዐምስት መጋረጃዎች እንደዚሁ አገጣጥመህ ስፋቸው።

4 ከዳር በኩል ባለው መጋረጃ ጠርዝ ላይ፣ ከሰማያዊ ጨርቅ የተሠሩ ቀለበቶች አድርግ፤ በሌላውም የመጋረጃ ጠርዝ ላይ እንዲሁ አድርግ።

5 ቀለበቶችን ትይዩ በማድረግ ዐምሳ ቀለበቶችን በአንደኛው ጠርዝ መጋረጃ፣ ዐምሳ ቀለበቶችንም በሌላው ጠርዝ መጋረጃ አድርግ።

6 ከዚያም የመገናኛው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድ መጋረጃዎቹን በአንድ ላይ ለማያያዝ ዐምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሥራ።

7 “ማደሪያ ድንኳኑን ከላይ ሆነው የሚሸፍኑ በጠቅላላ ዐሥራ አንድ የፍየል ጠጕር መጋረጃዎች ሥራ።

8 ዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች እኩል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ ርዝመት ሠላሳ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን።

9 ዐምስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ፣ እንደዚሁም ስድስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ አድርገህ ስፋቸው፤ ከማደሪያው ድንኳን ፊት ለፊት ስድስተኛውን መጋረጃ ዕጠፍና በላዩ ላይ ደርበው።

10 በአንድ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን አድርግ።

11 ከዚያም ዐምሳ የንሓስ ማያያዣዎችን ሥራ፤ ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝ በቀለበቶቹ ውስጥ ጨምራቸው።

12 ስለ ድንኳኑ መጋረጃዎች ትርፍ ቁመትም፣ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ላይ እንዲንጠለጠል ይሁን።

13 የድንኳኑ መጋረጃዎች በሁለቱም ጐኖች አንድ ክንድ ርዝመት ይኖራቸዋል፤ የተረፈውም የማደሪያውን ድንኳን ጐኖች እንዲሸፍን ሆኖ ይንጠለጠላል፤

14 ለድንኳኑ በቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ ልብስ አብጅ፤ በላዩም ላይ የአቆስጣ ቈዳ ይሁን።

15 “ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አብጅ።

16 እያንዳንዱም ወጋግራ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን፤

17 ሁለት ጕጦችም ጐን ለጐን ይሁኑለት፤ የማደሪያውን ድንኳን ወጋግራዎች ሁሉ በዚሁ መልክ አብጅ።

18 ለማደሪያው ድንኳን ክፍል በደቡብ በኩል ሃያ ወጋግራዎችን ሥራ።

19 ከሥራቸው የሚሆኑ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ፤ በእያንዳንዱ ጕጠት ሥር አንድ መቆሚያ ሲሆን፣ ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያዎች ይኑሩ።

20 በሌላው ጐን፣ ከማደሪያው ድንኳን በስተሰሜን በኩል ሃያ ወጋግራዎችን አብጅ፤

21 በእያንዳንዱም ወጋግራ ሥር ሁለት ሁለት መቆሚያ ሆኖ አርባ የብር መቆሚያዎችን አብጅ።

22 በዳር በኩል ለሚገኘው ይኸውም በምዕራብ ጠርዝ ላለው የማደሪያው ድንኳን ስድስት ወጋግራዎች አብጅ።

23 ዳርና ዳር ላሉት ማእዘኖች ሁለት ወጋግራዎች አብጅ።

24 በእነዚህ ሁለት ማእዘኖች ላይ ከታች እስከ ላይ ድረስ ድርብ ሲሆኑ፣ በአንድ ቀለበት ውስጥ የሚገጥሙ መሆን አለባቸው፤ በሁለቱም ወገን እንዲሁ መሆን አለበት።

25 ስለዚህ ስምንት ወጋግራዎች አሉ፤ እንዲሁም ዐሥራ ስድስት የብር መቆሚያዎች ሲኖሩ፣ ለእያንዳንዱ ወጋግራ ሁለት ሁለት መቆሚያ ይሆናል።

26 “ደግሞም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን አብጅ፤ በአንድ በኩል ላሉት የማደሪያው ድንኳን ወጋግራዎች ዐምስት፣

27 በሌላው ጐን ላሉት ዐምስት፣ በማደሪያው ድንኳን ዳር በምዕራብ በኩል ባሉት ወጋግራዎች ዐምስት አብጅ።

28 መካከለኛው አግዳሚ በወጋግራዎቹ መካከል ከጫፍ እስከ ጫፍ ይተላለፍ።

29 ወጋግራዎቹን በወርቅ ለብጣቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝ የወርቅ ቀለበቶች አብጅ፤ አግዳሚዎቹንም በወርቅ ለብጣቸው።

30 “ማደሪያ ድንኳኑንም በተራራው ላይ ባየኸው ዕቅድ መሠረት ትከለው።

31 “ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ ሥራ፤ እጀ ጥበብ ባለሙያም ኪሩቤልን ይጥለፍበት።

32 በወርቅ በተለበጡ ከግራር ዕንጨት በተሠሩና በአራቱ የብር መቆሚያዎች ላይ በቆሙት በአራቱ ምሰሶዎች፣ በወርቅ ኵላቦች ላይ አንጠልጥለው።

33 መጋረጃውን በማያያዣዎቹ ላይ ስቀለው፤ የምስክሩንም ታቦት ከመጋረጃው በስተኋላ አስቀምጠው፤ መጋረጃውም መቅደሱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ይለያል።

34 በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ በምስክሩ ታቦት ላይ የማስተስረያውን ክዳን አስቀምጥ።

35 ጠረጴዛውን ከመገናኛው ድንኳን በሰሜን በኩል ከመጋረጃው ውስጥ አስቀምጠው፤ መቅረዙንም ከርሱ ትይዩ በማድረግ በደቡብ በኩል አድርገው።

36 “ለድንኳኑ ደጃፍ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ በጥልፍ ዐዋቂ የተጠለፈ መጋረጃ አብጅ።

37 ለዚህም መጋረጃ የወርቅ ኵላቦችንና ከግራር ዕንጨት የተሠሩ፣ በወርቅ የተለበጡ ዐምስት ምሰሶዎችን አብጅ፤ ዐምስት የንሓስ መቆሚያዎችንም አብጅላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告